መንግስት፤በአማራ ክልል ከህግ አግባብ ዉጪ የሚደረግ ግድያ እንዲያስቆም እና ጥፋተኞችንም ለፍርድ እንዲያቀርብ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ባወጣዉ መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር በንጹሃን ላይ ከህግ አግባብ ዉጪ ግድያ መፈጸማቸዉን እና የሟች ቤተሰቦችም አስከሬናቸዉን ለመቅበር ፍቃድ አለማግኘታቸዉን ገልጿል፡፡

መግለጫዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በባህርዳር ከተማ ቀበሌ 14 አቡነ ሃራ እና ልደታ በተባሉ ሰፈሮች ዉስጥ 6ንጹሃን ዜጎችን በፈረንጆቹ ነሀሴ 8 2023 ከህግ አግባብ ዉጪ መግደላቸዉን ያሳያል፡፡

ይህ ግድያ ከተፈጸመ ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ ሰባ ታሚት በተባለ ሰፈር ዉስጥ 5 ንጹሃንን ጨምሮ 6 ሰዎችን መግደላቸዉን አስታዉቋል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግስት በክልሉ እየተካሄደ ያለዉን የትጥቅ ግጭት ምክንያት በማድረግ የሚደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ገለልተኛ በሆነ አካል ምርመራ እንዲደረግበት በአስቸኳይ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት ብሏል፡፡

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ቲግረ ቻጉታህ ፤ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለዉ የትጥቅ ግጭት ምክንያት በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኢንተርኔት መዘጋት እንዲሁም ከፊል ግንኙነቶች በመኖራቸዉ የሚገባዉን ያህል ትኩረት እንዳልተሰጠዉ በማንሳት ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ደግሞ የመናገር እና የሚዲያዉን ነጻነት የሚጋፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለዉም የኢትዮጵያ መንግስት በክልሉ እየተካሄደ ባለዉ የትጥቅ ግጭት ምክንያት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በገለልተኛ አካል እንዲጣራ በአስቸኳይ ሁኔታዎችን ያመቻች ያሉ ሲሆን፤ በቂ ማስረጃዎችን በማቅረብ፣ በጉዳዩ የተጠረጠሩ አካላትም ደግሞ ዓለምዓቀፋዊ የፍርድ ስርዓቶችን በተከተለ መንገድ እንዲዳኙ ጠይቀዋል፡፡

አለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ህጎችን የሚጣረሱ የትኛዉም ጥፋቶች የጦር ወንጀሎች ተብለዉ እንደሚቀመጡ የተነሳ ሲሆን ፤ ከህግ ዉጪ የሚደረጉ ግድያዎችም በዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ህግ የተደነገገዉን የመኖር መብትን የሚጥስ በመሆኑ ከጦር ወንጀል የሚታሰብ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ዳይሬክተሩ ፤በኢትዮጵያ አሁን ላይ በስፋት የሚታየዉ ተዓማኒ የሆነ ፍትህ አለመስጠት እና ተጠያቂነት የሌለበት እስር ወንጀለኞች ተገቢዉን ፍርድ ሳያገኙ ጉዳዩ ተድበስብሶ እንዲያልፍ ዕድል የሚሰጥ ነዉ ያሉ ሲሆን፤ በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣዉን ይህን ተገቢዉን ፍትህ ያለማግኘት እና ተጠያቂነት የሌለበትን አሰራር ለማቆም ጊዜዉ አሁን ነዉ ብለዋል፡፡

አትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply