መንግስት ሕገ-መንግስቱን ያክብር አለ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ኢሕአፓ ፡፡የኢሕአፓ ሊቀመንበርና ሌሎችም የኅሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ይፈቱ ሲል ኢህአፓ በዛሬው ዕለት ባ…

መንግስት ሕገ-መንግስቱን ያክብር አለ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ኢሕአፓ ፡፡

የኢሕአፓ ሊቀመንበርና ሌሎችም የኅሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ይፈቱ ሲል ኢህአፓ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡

ፓርቲው ለጣብያችን ኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ ኢትዮጵያ አንደ አገር እንድትቀጥል በአገራችን ውስጥ የሕግ የበላይነት ሊኖር ይገባል ብሏል።

የመንግሥት አካላት ዜጎችን እንደፈለጉ ማሰር፣ መግደል፣ ማፈናቀል፣ መደብደብ፣ ማፈን፣ ማንገላታት፣ ማሳደድ፣ ቤት ንብረታቸውን መቀማት ከጀመሩ መንግሥትንና ሕዝቡን የሚያስተሳስረው ሕግዊ ሥርዓት ትርጉም-አልባ ሆኗል የሚለው መግለጫው። መንግሥት በቅድሚያ ሕገ-መንገስት ስርዓቱን ሊያከብር ይገባል ብሏል፡፡

ከዚህ ውጪ መንግስት ስለ ጦርነት መቆምና ሠላም መስፈን ጥያቄ የሚያነሱትን ወገኖች እያሰረ ይገኛል ሲል ተችቷል በመግለጫው፡፡

ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ .ም ሊጠራ ታስቦ የነበረው ሠልፍ ዋናው ጥያቄ “ጦርነት ይቁም፣ ሰላም ይስፈን” የሚል የነበር ቢሆንም በከፍተኛ የሀገርና የወገን ፍቅር ተነሳስተው ሠላማዊ ሠልፉን ለመጥራት የሞከሩትን የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችና አባሎች መንግሥት ከህዳር 27 ቀን 2016 ዓ. ም ጀምሮ በማሰርና በማንገላታት ላይ ነው ይህም ዛሬም እየተስተዋለ ነው ብሏል ኢህአፓ ፡፡

ከሦስት ወር ተኩል የአዋሽ አርባ እስርና እንግልት በኋላ የፓርቲያችን ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር መጋቤ ብሉይ አብርሃም ኃይማኖትና ጊደና መድሕን ቢፈቱም፣ በወቅቱ ከታሠሩት ውስጥ አቶ ናትናኤል መኮንን እስከዛሬ አለመፈታቱ እንዳለ ሆኖ፣ ሌሎችንም ሰልፉን ለመጥራት እንደ የኢሕአፓ ሊቀመንበር፣ ረ/ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ ያሉት መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ. ም ጀምሮ ታስረው ይገኛሉ ብሏል፡፡

መንግስት ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ማኅበራዊ አንቂዎችን፣ ሌሎችንም ዜጎች እስር በአስቸኳይ እንዲያቆም በመግለጫው ጠይቋል፡፡

የኢሕአፓ ሊቀመንበር ረ/ፕ ዝናቡ አበራም በአስቸኳይ ይፈቱ ሲል ለጣብያችን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

አቤል ደጀኔ

ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply