You are currently viewing ''መንግስት ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን በአግባቡ ያክብር'':- ኢሰመጉ የኢሰመጉ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ:-  ሰኔ 22 / 2014 በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምዕራብ ወለጋ ዞን…

''መንግስት ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን በአግባቡ ያክብር'':- ኢሰመጉ የኢሰመጉ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ:- ሰኔ 22 / 2014 በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምዕራብ ወለጋ ዞን…

”መንግስት ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን በአግባቡ ያክብር”:- ኢሰመጉ የኢሰመጉ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ:- ሰኔ 22 / 2014 በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሚዥንጋ ወረዳ ሴነ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በሸኔ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት እጅግ በጣም በርካታ ንጹሀን ሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ንብረት ውድመት፣ ዘረፋ እና እገታዎች መፈጸማቸውን እንዲሁም ኢሰመጉ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም መግለጫ በማውጣት መንግስት የእርምት እርምጃዎችን በመውሰድ ጥፋት አድራሾችን ለህግ እንዲያቀርብ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ በዚህ ጥቃት ምክንያት በርካታ ሰዎች(በዋናነት ህጻናት) ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች(በተለይም ህጻናት) እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እና ይህ እርዳታ እና ድጋፍ በበቂ ሁኔታ እየደረሰ አለመሆኑን ኢሰመጉ ከአካባቢው ባሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ ይህንን ድርጊት በማውገዝ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላማዊ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን ሰኔ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ጊዎን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምናና ጤና ሳይንስ ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፎችን ያደረጉ ቢሆንም ሰልፎቹ የጸጥታ ሀይሎች አስለቃሽ ጭስንና ሀይልን በመጠቀም እንደበተኑት እና በሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች በነበሩ ሰልፎች ላይ የተደበደቡ እና የታሰሩ ተማሪዎች እንደሚገኙ ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ ተያያዥ የህግ ግዴታዎች፡ የሲቪል እና ፖለቲካል መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 21 ላይ ሰዎች ሰላማዊ ስብሰባ የማድረግ መብት እንዳላቸው እና ለብሔራዊ ጸጥታና የህዝብ ሰላምና ደህንነት ጥቅም ወይም የህዝብን ጤናና ስነ ምግባር ለመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብቶችና ነጻነቶች ለማስከበር ከሚያስፈልገውና በህግ ከተደነገገው በቀር በዚህ መብት ላይ ምንም ገደብ አይደረግም ሲል ይደነግጋል፡፡ በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች ላይ የወጣው የአፍሪካ ቻርተር በአንቀጽ 11 ላይ ሁሉም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን የመሰብሰብ መብት እንዳለው እና ይህ መብት ሊገደብ የሚችለው በህግ አግባብ በተደነገገው መሰረት ብቻ ለብሄራዊ ጸጥታ፣ ደህንነት፣ ጤና፣ ስነ ምግባር፣ እና ለሌሎች ነጻነቶች እና መብቶች ብቻ እንደሆን ይደነግጋል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 30 ላይ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትንና አቤቱታ የማቅረብ መብት በማለት ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ከእነዚህ ህጎች እና ከዓለም አቀፍ የህግ ፍልስፍና (jurisprudence) ልንረዳ የምንችለው ማንም ሰው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እንዳለው እና ይህንንም መብት ለመለማመድ ለመንግስት የማሳወቅ ስራ መስራት ብቻ በቂ እንደሆነ (ፈቃድ የሚለው እሳቤ ትክክለኛ አረዳድ እንዳልሆነ) እንዲሁም ከላይ ከተጠቀሱት የተወሰኑ ሁኔታዎች በስተቀር ይህ መብት እንደማይገደብ ነው፡፡ የኢሰመጉ ጥሪ፡ – መንግስት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሚዥንጋ ወረዳ ሴነ ቀበሌ ውስጥ የተፈጸመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በመመርመር ጥሰት ፈጻሚዎችን ለህግ እንዲያቀርብ፣ ሰብዓዊ ድጋፍን (ምግብ፣ ውሀ፣ አልባሳት፣ የህክምና ቁሳቁስና አገልግሎት እና ሌሎችንም) በዚህ ጥቃት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርብ እና ይህ ድጋፍ ሴቶች፣ ህጻናት እና አካል ጉዳተኞች የሚያስፈልጋቸውን ትኩረት ከግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን፣ – የዜጎችን የመሰብሰብ መብት ማለትም ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን እንዲያከብር እና እንዲያስከብር፣ – ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ በነበሩ ተማሪዎች ላይ ድብደባ እና እንግልት የፈጸሙ አካላትን ለህግ በማቅረብ ተጠያቂ እንዲያደርግ እና በጸጥታ አካላት የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ተግባሮችን በአስቸኳይ እንዲያስቆም፣ – በዚህ ሰልፍ ምክንያት ታስረው የሚገኙ ሰዎችን የአካል ነጻነታቸውን እንዲያከብር እንዲሁም ተገቢውን ማጣራት በማድረግ አፋጣኝ ፍትህ እንዲሰጥ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ሰ.አሜሪካ:- ሰኔ 22/2014 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply