መንግስት በተለያዩ የወለጋ አካባቢዎች በንጹሃን ላይ እየተፈፀመ ያለውን ጭፍጨፋ በአፋጣኝ እንዲያስቆም አብን ጠየቀ፡፡የፌደራል መንግስት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የወለጋ አካባቢዎች በንጹሃን…

መንግስት በተለያዩ የወለጋ አካባቢዎች በንጹሃን ላይ እየተፈፀመ ያለውን ጭፍጨፋ በአፋጣኝ እንዲያስቆም አብን ጠየቀ፡፡

የፌደራል መንግስት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የወለጋ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግድያ በአፋጣኝ እንዲያስቆም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠይቋል።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የወለጋ አካባቢዎች የአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ያለው ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እና እየሰፋ እንደሚገኝም ፖርቲው ገልጿል።

“የኦሮሚያ ክልል መንግስት በወለጋ እና ሌሎች አካባቢዎች በንፁሃን ላይ እየተፈፀመ ያለውን ጭፍጨፋ፣ ማፈናቀል፣ እገታ እና ንብረት ዝርፊያ ለማስቆም ፍላጎት እና አቅም እንደሌለው በተደጋጋሚ ጊዜ ታይቷል፣ ቀላል የማይባለው የክልሉ መዋቅርም የጭፍጨፋው ተሳታፊና ሽፋን ሰጭ ሆኗል።” ያለው አብን፤ ጭፍጨፋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቶ በዚህ ሳምንት እጅግ አደገኛ ወደ ሆነ ደረጃ መሸጋገሩን አስታውቋል።

“የክልሉ መንግስት ክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ማንነት፣ ዘር እና ኃይማኖት ሳይለይ እኩል የመጠበቅ እና ከለላ የመስጠት መንግስታዊ ግዴታውን መወጣት ሳይችል ቀርቶ የአማራ ተወላጆች በተለይ የመከራ ዶፍ እየወረደባቸው ይገኛል።”ያለው ፓርቲው፤ ስለሆነም የፌደራል መንግስት በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለውን የዘር ጭፍጨፋ በአስቸኳይ ጣልቃ ገብቶ ማስቆም እና ጥፋተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል ሲል በጥብቅ አሳስቧል።

የፌደራል መንግስት በኦሮሚያ ክልል አመራሮች ላይ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያሳሰበም ሲሆን፤ የወገኖቻችንን ሕይወት ለመታደግ ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ባለባቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሠራዊት በፍጥነት ማሰማራት እንዳለበትም አሳስቧል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ ዝርዝር መረጃ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝም በመግለጽ፣ በቅርቡም ሰፋ እና ዘርዘር ያለ መግለጫ የሚያወጣ መሆኑን አሳውቋል። አክሎም፤ ችግሩ በፍጥነት እልባት እንዲያገኝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚችለውን ሁሉ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጿል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ወቅታዊ አዳዲስ መረጃዎችና ፕሮግራሞችን ለማግኘት ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

Twitter https://twitter.com/EthioFM

YouTube https://www.youtube.com/…/UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/videos

Facebook https://www.facebook.com/onelovebroadcast

Website https://ethiofm107.com/

ያሎትን አስተያየት እና ጥያቄ በአጭር መልዕክት 6321 ላይ ይላኩልን።
ከኛ ጋር ስለሆናችሁ ከልብ እናመሰግናለን።

Source: Link to the Post

Leave a Reply