መንግስት በአምስት ወራት ውስጥ ብቻ በድሮን 248 ንጹሀንን ገድሏል- የመንግስታቱ ድርጅት

ዓርብ ሰኔ 07 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ከፈረንጆቹ ጥር 2023 እስከ ጥር 2024 ገምግሞ ሪፖርት አውጥቷል።

ለሁለት ዓመታት በጦርነት ስር የቆየው ትግራይ ክልል ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ በሰብዓዊ መብት አያያዝ የተሻለ ቢሆንም በሰሜናዊ ትግራይ አሁንም የኤርትራ ሠራዊት ጥሰት እያደረሰ ነው ተብላል።

የተመድ የመብቶች ቢሮ እንዳስታወቀው በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው። ከጥር 2015 እስከ ጥር 2016 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 1 ሺህ 351 ንጹሀን ዜጎች በመንግስት ኃይሎች፣ በኤርትራ ሠራዊት፣ የመንግስት ተቃዋሚ ታጣቂዎች እንዲሁም ባልታወቁ አካላት ተገድለዋል ያለው ሪፖርቱ፤ ከዚህ ውስጥ 740 የሚሆኑት በአማራ ክልል ውስጥ የተገደሉ ናቸው ሲል ገልጿል።

በተጨማሪም የፌደራሉ መንግስት ከሐምሌ 28 ቀን 2015 እስከ ታህሳስ 21 ቀን 2016 ድረስ ባሉት አምስት ወራት ውስጥ በሰው አልባ በራሪ የጦር መሳሪያዎች 248 ንጹሀን ዜጎችን ገድሏል ያለው የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ፤ የጤና እና የትምህርት ተቋማትንም ያወደመ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ሕግ የሚያስጠይቅ ይሆናሉ በማለት አስታዉቋል።

በጠቅላላ በአገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ካለፈው የፈረንጆች ሙሉ ዓመት በ56 በመቶ የጨመረ እንደሆነ ተገልጿል። ከነዚህ የመብት ጥሰቶች ውስጥ የመንግስት ኃይሎች 70 በመቶ ድርሻ ሲኖራቸው 22 በመቶ የሚሆኑት መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት እንደሆኑ ተገልጿል።

ከቀናት በፊት የተጠናቀቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስካሁን አለመራዘም የመብቶች ቢሮው ያደነቀ ሲሆን መሬት ላይም በተግባር እስረኞች በሕግ አግባብ የሚታዩበት እና መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲሁም የሕግ ሂደት እንዲኖር የኢትዮጵያ መንግስትን አሳስቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply