መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት እና የኢንተርኔት ጉዳይ እቀባ ላይ የተፈጠረው ጫና ላይ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጥ ይገባዋል ሲል ኢሰመጉ ጠየቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በወቅታዊ ጉዳይ ባሰጣው መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በክልል ከተሞች እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ መምጣቱን አመላክቷል። ይህም ማህበረሰቡ የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት፣ የቁሳቁስ፣ የህክምና፣ የነዳጅና የትምህርት ወጪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ከመናራቸውም አልፎ የእለት ጉርሱን በአግባቡ እንዳያገኝ ተግዳሮት እየሆነበት ይገኛል ብሏል፡፡ የኑሮ ውድነቱን ከሚያባብሱት ምክንያቶች አንዱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱት ግጭቶች ምክንያት የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ማለትም አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶች እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞች ንብረታቸው በመውደሙ እና እንዲሁም ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ መደገጉ ነው ብሏል። ይህም አምራቹን እና መስራት የሚችለውን የማህበረሰብ ክፍል ስራ አጥ እና እርዳታ ፈላጊ እንዲሆን ማድረጉ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለው ድርቅ እርዳታ የሚፈልጉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመጨመሩና ተመጣጣኝ የሆነ የምግብ እህል አቅርቦት እንዳይኖር ያደረገ ስለመሆኑ ገልጧል። በሌላ በኩል በአማራ፣ በኦሮምያና ሌሎችም ክልሎች የስንዴ እና ጤፍ አምራች የሆነ አርሶ አደር ያመረተውን ምርት:_ 1) በቀጥታ ለሸማች ወይም ለተጠቃሚ ማህበረሰብ እንዲቀርብ አለመደረጉ፣ 2) መንግስት ባስቀመጠው የዋጋ ተመን መሰረት ለማህበሮች እንዲሸጡ መደረጉ፣ 3) አምራቹ አርሶ አደር ከሸማቹ ጋር በቀጥታ ባለመገናኘቱ እና በነጻ ገበያ ተጠቃሚ ባለመሆኑ በማምረት ሂደቱ የሚያወጣቸውን ወጪዎች ማለትም ማዳበሪያና ዘር የገዛበትን ለመሸፈን እንኳን በቂ አለመሆኑ፣ 4) ያመረተውን እህል ለገበያ ባለማውጣቱ የእህል አቅርቦት ችግር እንዲፈጠርና ማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እህል መግዛት እንዳይችል እያደረገ መሆኑን ጠቅሷል። በሌላ በኩል ከእህል አቅርቦት ችግር በተጨማሪ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ፣ የገበያ ስርዓት መዛባቱ ይህም ማለት ለገበያ የሚቀርቡት እቃዎችም ሆነ ሸቀጣ ሸቀጦች በተመጣጠነ መልኩ እኩል ተደራሽ አለመሆናቸው የኑሮ ውድነቱን እንዳባባሰው ገልጧል። በተጨማሪም የነዳጅ የህክምና፣ የትምህርት ቤት ክፍያ፣የቤት ኪራይ፣ ሸቀጣ ሸቀጥ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ በየጊዜው እየተደረገ ያለው የዋጋ ጭማሪ የኑሮ ውድነቱን እያባባሰ የመጣ ጉዳይ መሆኑን ኢሰመጉ ተረድቷል፡፡ በተያያዘም ከየካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ቴሌግራም፣ ፌስቡክ እንዲሁም ሌሎች የትስስር ገፆች ላይ መንግስት ገደብ መጣሉን አውስቷል። አሁንም ይህ ገደብ እንደቀጠለ በመሆኑ ሰዎች መረጃ የማግኘት፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ገደብ የሚጥልና የሚጋፋ ከመሆኑም በተጨማሪ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ብሏል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት መንግስት በኢንተርኔት ግንኙነት የጣለው ገደብ ሚዲያዎች ስራቸውን በአግባቡ ለህዝብ ተደራሽ እንዳያደርጉ እንቅፋት እየፈጠረ በመሆኑ ገደቡ ሊነሳ ይገባል የሚል መግለጫ ያወጣ ቢሆንም እስከአሁን ገደቡ ቀጥሎ ይገኛል ሲል አክሏል፡፡ ተጠቃሚዎችም ገበያ ላይ በተገኘ በማንኛውም ቨርችዋል ፕራይቬት ኔትወርክ (VPN) ለመጠቀም በመገደዳቸው ምክንያት የመረጃዎችን ደህንነት ጉዳይ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብሏል ኢሰመጉ በመግለጫው።
Source: Link to the Post