መንግስት በዘር ማጥፋት ወንጀል መጠየቅ የሚገባቸውን አካላት ምህረት በሚል ከህሊና እስረኞች ጋር አብሮ መፍታቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ቅሬታ እያስነሳበት ነው። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህ…

መንግስት በዘር ማጥፋት ወንጀል መጠየቅ የሚገባቸውን አካላት ምህረት በሚል ከህሊና እስረኞች ጋር አብሮ መፍታቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ቅሬታ እያስነሳበት ነው። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ እንዲሁም በሌሎች ንጹሃን ወገኖቻችን ጭምር አሰቃቂ የጅምላ ፍጅት እንዲፈጸም አድርገዋል የተባሉትን ጃዋር መሀመድ፣ ስብሃት ነጋ እና ሌሎችንም ታህሳስ 29 ቀን 2014 መፍታቱ በብዙዎች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል። የግፍ እስረኞቹ እነ እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሌ የመፈታታቸው ዜና ካስደሰታቸው በተቃርኖ በዘር ማጥፋት ወንጀል መጠየቅ ያለባቸው የትሕነግ እና ኦነግ ቀንደኛ አመራሮች፣ በጥላቻ እና በሀሰት ትርክት የተካኑት ተጃምለው መፈታታቸው በፍትህ ፈላጊ እና ወዳድ ወገኖች ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገር ላይ የተፈጸመ ክህደት ስለመሆኑ የገለጹ ብዙዎች ናቸው። የመንግስት ውሳኔን በግልጽ ከተቃወሙት መካከል የታሪክ ተመራማሪው አቻምየለህ ታምሩ እና ፖለቲከኛ መልካሙ ሹምዬ ይገኙበታል። አቻምየለህ ታምሩ እንዲህ ሲል የጠ/ሚኒስትሩን አካሄድ ይቃወማል:_ “ዐቢይ አሕመድ መከላከያ ሠራዊቱ ያንን ሁሉ የሕይዎት መስዕዋትነት ከፍሎ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን የጦር ወንጀለኞቹን እነ ስብሀት ነጋን በነጻ በመልቀቅ በሠራዊቱ ላይ የፈጸመው ክህደት ፋሽስት ወያኔ በሰሜን ዕዝ ላይ “መብረቃዊ ጥቃት” በማድረስ ከፈጸመው ክህደት የማይተናነስ ነው።” በተጨማሪም “አሁንም ደግሜ ለኢትዮጵያውያን ላረጋግጥላችሁ የምወደው የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራችን ሳይጠናቀቅ ከዚህ ጁንታ ጋር ድርድር እንደማይኖር ነው።” ያለው ሰውየ ዋነኛውን ጁንታና የጦር ወንጀለኛውን ስብሐት ነጋን በምህረት ከእስር እንደፈታው ነግሮናል” ሲል አውግዟል። አቻምየለህ ሲቀጥል “የሕግ ማስከበሩና ፍትሕ የተጓደለባቸው ሁሉ ፍትሕ ስላገኙ ነው ወንጀለኞቹ ሳይፈረድባቸው ቆይተው የተለቀቁት? ሌላው ቀልድ ደግሞ በምህረት ተለቀቁ መባሉ ነው። መቼ ተፈረደባቸውና ነው በምህረት የሚለቀቁት? የሚያሳዝነው እነ ስብሀት ነጋን ለመያዝ ያ ሁሉ የኢትዮጵያ ወጣት ማለቁ ነው።” ሲልም በግልጽ ተቃውሟል። በመጨረሻም “እነ ስብሀት ነጋን ለመያዝ በለጋ እድሜያቸው የተቀጩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ባለ ደም እነ ስብሀት ነጋና ድርጅታቸው ፋሽስት ወያኔ ሳይሆን በግፉዓን ነፍስ የሚቀልደው ዐቢይ አሕመድ ነው። ስለሆነም በነዚያ ወጣቶች ሕይዎት ሕመምተኛው ዐቢይ አሕመድ መጠየቅ አለበት።” ሲል ሀሳቡን አጠቃሏል። በተያያዘ ፖለቲከኛ መልካሙ ሹምዬ በበኩሉ “በመላው ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም በአማራ ደም የተጨማለቁ ወንጀለኞች እንዲፈቱ ሊወሰን የሚችለው በብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔ ነው።” ብሏል። “የአማራ ብልፅግና ሰዎች ውሳኔውን ባይቀበሉት (አንዳንዶቹ በግልፅ የሃሳቡ አቀንቃኞችም ናቸው) ኖሮ በተናጠልም ሆነ በቡድን ውሳኔውን ከመቃወም ማንም አይከለክላቸውም ነበር” ሲልም ገልጧል። “በእኔ እምነት እነሱም አምነውበት የተፈፀመ ውሳኔ ነው፤ ካልሆነ በቡድንም ሆነ በግል በግልፅ ውሳኔውን ኮንነው resign ሲያደርጉ ወይም ደግሞ እንደ chapter ሲወጡ ማየት ነበረብን” ያለው መልካሙ “ከዝንጀሮ ቆንጆ መካከል ውቢቷን ለመምረጥ አንሞክር፤ ውሳኔው የጋራ ነው፤ ትግሉም በሁሉም ላይ መሆን አለበት” ሲልም አክሏል። “አንዳንዶች ፍጹም አምነናቸው ነበር፣ ከዱን፣ አሞኙን በማለት እያለቃቀሱ ነው፤ በፖለቲካ ዓለም ጥቅምህን መሰረት አድርገህ ትደጋገፋለህ፣ መደጋገፉ ሲቀር ወይም ከአንተ ጋር ሲደጋገፍ የነበረው ከሌላው ጋር መደጋገፍ ሲጀምር አንተም የቆምክለትን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል እንቅስቃሴ ውስጥ ትገባለህ፤ ሌላ አማርኛ የለውም” ነው ያለው። መልካሙ ሲቀጥል “ግልፅ የሆነው ነገር የለየላቸው ጸረ-አማራ ኃይሎች ጥምረት መፍጠር የሚችሉበት እድል እየመጣ መሆኑ ነው፤ ይህ እውን እንዲሆን በሕዝብ ላይ የጭካኔ ወንጀል (ጭፍጨፋ) የፈፀሙ ሁሉ እንዲፈቱ ተደርጓል፤ ፍትሕ በአደባባይ ተደፍጥጧል፤ እኛ እየኮነን ያለነው ይህን እርምጃ ነው፤ ለማንኛውም አማራን በጥላቻና በጥርጣሬ የሚመለከቱ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የድርሰቱ ባለቤት እንደሆኑ አምናለሁ” ሲል እይታውን አጋርቷል። መልካሙ በመጨረሻም መፍትሔ ያለውን ሀሳብ አስፍሯል። “ጩኸትና ተናካሽነትን ቀነስ፣ ስክነትና አርቆ አሳቢነትን ጨመር አድርጎ አቅምን አሰባስቦ መቆም ላይ ርብርብ ማድረግ ይገባል። የራሳችን አቅም ግዙፍ ቢሆንም ብዙ ስትራቴጃዊ አጋሮችም አሉን። ከእነርሱ ጋር በጋራ ደኅንነትና ጥቅም መርኅ መስራት ይገባል” ሲል ነው ሀሳቡን በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ ያጋራው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply