”መንግስት የሰዎችን በአገር ውስጥ የመዘዋወር መብት ያክብር፣ ያስከብር!” :- ኢሰመጉ

አርብ ነሐሴ 6 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) መንግስት የሰዎችን በአገር ውስጥ የመዘዋወር መብት ያክብር፣ ያስከብር ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አሳሰበ።

ኢሰመጉ ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚመጡ ትራንስፖርት ተጠቃሚ የሆኑ መንገደኞች በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ባሉና፤ በዋናነት በሸኖ፣ አለልቱ፣ በኪ፣ ሰንዳፋ እና ለገጣፎ አካባቢ በሚገኙ የፍተሻ ጣቢያዎች መታወቂያቸው እየታየ ወደመጡበት እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑንና በዚህም ዜጎች ከፍተኛ የሆነ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች እንደደረሱት ገልጿል፡፡

ይህ ህገ-ወጥ የሆነ ድርጊት አንድ ወር የሆነው ሲሆን፤ በአንዳንድ የፍተሻ ኬላዎች ላይ ለማለፍ ተገቢ ያልሆነ ገንዘብ መንገደኞች እየተጠየቁ እንደሆነ፣ የአዲስ አበባ ወይም የኦሮሚያ መታወቂያ የሌለው ማለፍ እንዳልቻለ ከዚህም ጋር ተያይዞ ለተለያዩ ጉዳዮች ህክምናንም ጨምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ መንገደኞች ያለአግባብ እየተንገላቱ መሆኑን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችያለሁ ብሏል፡፡

ይህንንም አስመልክቶ ኢሰመጉ ለሰላም ሚኒስቴር እና ለትራንስፖርት ሚኒስቴር በደብዳቤ ቁጥር ER1-m41/59/22 ነሐሴ 03 ቀን 2014 የጽሁፍ ማብራሪያን መጠየቁን የገለጸ ሲሆን፤ ነሐሴ 04 ቀን 2014 የወልዲያ ደሴ አዲስ አበባ መስመር ከደብረ ብርሀን ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ መዘጋቱን እና ምንም አይነት ትራንስፖርት ማለፍ አለመቻሉን ነገር ግን መንገዱ ሙሉ ለሙሉ ነሐሴ 05 ቀን መከፈቱን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት መቻሉን በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ስለሆነም ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር ኢሰመጉ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹን ምላሽ ሳያካትት ይህንን አስቸኳይ መግለጫ መንግስት ፈጣን ማስተካከያ እንዲያደርግ ለማሳሰብ ማውጣቱን በመግለጽ፤ ወደፊት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹን ምላሽ በማካተት በጉዳዩ ዙሪያ ሰፋ ያለ ዘገባን እንደሚያዘጋጅ ገልጿል፡፡

ከዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና አገር አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች እንደምንረዳው መንግስት የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች ማክበር፣ ማስከበር እና የማሟላት ሀላፊነት አለበት ያለው ኢሰማጉ፤ ይህ ሳይሆን ሲቀር እና በመንግስት ቸልተኝነት የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ሳይከበሩ ሲቀሩ ዋነኛ ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው መንግስት ነው ብሏል፡፡

በዚህም መሰረት፤ መንግስት ከተለያዩ የአማራ ክልል ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ መንገደኞችን የመንቀሳቀስ መብት እንዲያከበር እና እንዲያስከብር፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካል በአፋጣኝ ለዚህ ችግር ዘላቂ መፈትሔን በማበጀት ሰዎች በአገራቸው የመንቀሳቀስ መብታቸውን እንዲያከብር እንዲሁም እንዲያስከብር አሳስቧል።

በተጨማሪም በተለያዩ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የፍተሻ ጣቢያዎች ላይ መንገደኞችን የሚያጉላሉ፣ አላግባብ ገንዘብ የሚቀበሉ፣ የሚደበድቡ እና የሚያስሩ የጸጥታ አካላትን ተገቢውን ምርመራ በማድረግ መንግስት በህግ ተጠያቂ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ – (ኢሰመጉ) ጠይቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply