መንግስት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ላይ በሰጡት አስተያየት ማብራሪያ ጠየቀ

መንግስት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ላይ በሰጡት አስተያየት ማብራሪያ ጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይነርን በጽህፈት ቤታቸው አስጠርተው ማብራሪያ ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ማይክ ሬይነርን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው አስጠርተው ፕሬዚዳንት ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ላይ በሰጡት አስተያየት ዙሪያ ነው ማብራሪያ የጠየቁት።

ትረምፕ ከሱዳን እና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባቷ አግባብ አለመሆኑን እና ግብፅም ግድቡን ልታፈርሰው እንደምትችል እንዲሁም ሀገራቸው የጀመረችውን እርዳታ ማቋረጧን እንደምትገፋበት አስተያየት ሰጥተዋል።

አቶ ገዱ በዚሁ ወቅት ፕሬዝዳንት ትረምፕ በግድቡ እና በሶስትዮሽ ድርድሩ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት የተሳሳተ ነው ብለዋል።

አቶ ገዱ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአባይን ውሃ ፍሰት እንደማያቆም እየታወቀ ፕሬዝዳንቱ የሰጡት መግለጫ ሰዎችን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ የሚመራ እና በድርድር ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳደር በመሆኑ አላስፈላጊ ነው ብለዋል።

የፕሬዚዳንቱ ንግግር አሜሪካንን እየመራ ካለ እና ሃላፊነት ከሚሰማው ፕሬዝዳንት የማይጠበቅ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ጦርነት ቀስቃሰሽ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነት እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የሚያንፀባርቅ አይደለም ብለዋል አቶ ገዱ።

እንዲሁም ሉዓላዊ አገሮች በሚመሩበት በየትኛውም ዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
ከዚያም ባለፈ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ በሚሰነዘሩ በየትኛውም አገር ዛቻዎች እንደማትንበረከክ እና ወደፊትም መሰል ንግግሮች ተቀባይነት እንደሌላቸውአቶ ገዱ ለአምባሳደሩ አስታውቀዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ የተጀመረውን የሶስትዮሽ ድርድር ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኗንም አቶ ገዱ ከአምባሳደር ማይክ ራይነር ጋር በነበራቸው ውይይት በአጽነኦት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

The post መንግስት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ላይ በሰጡት አስተያየት ማብራሪያ ጠየቀ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply