
መዋቅራዊ ድጋፍ ያለው አሸባሪው ኦነግ ሸኔ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ግንቦት 6 ቀን ተኩስ ከፍቶ እንደነበር ተገልጧል፤ ለተሻለ የተናበበ ትግልም መከላከያ እና የደራ ወረዳ አመራሮች የአማራ ሚሊሾችን እየፈረጁ ማሰር እና ማሳደዳቸውን እንዲያቆሙ ተጠይቋል። የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ግንቦት 9/2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ በደራ አቦቴ ጨለንቆ አካባቢ በመከላከያ ሰራዊት አባላት እና በኦነግ ሸኔ መካከል ግንቦት 6/2015 የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል። የሸኔ ሽብር ቡድን ሸሽቶ በጀማ አካባቢ በከፍተኛ ቁጥር የገባ እና ከጀማ ማዶ ሸንበቆ ጀማን ሳይሻገር ደራ ውስጥ ቀሪሶ በሚባል ቦታ ድንኳን ተክለው የተቀመጡ መሆኑን የአሚማ ምንጮች ገልጸዋል። ቡድኑ በመንቃታ እና በባቡ ድሬ አካባቢም በብዛት ታይተዋል፤ በያዝነው ሳምንት ጃርሶ ዱለታ የሚባል አካባቢ ከ700 በላይ አዲስ ምልምል ሰራዊት ያስመረቀ መሆኑም ተገልጧል። ይህ ኃይል የጀማን ወንዝ ተከትሎ ወደ ደራ የገባ ሲሆን የሚያሳዝነው ግን የደራ ወረዳ አንዳንድ ካቢኔ አባላት የደራ ሚሊሻ ጠላትን እንዳይከላከል የተለያየ ስምና ፍረጃ በመስጠት የውጊያ ሞራል እንዲያጣ እየሰሩ ነው ተብሏል። አብዛኞቹን የሚሊሻ አባላት የፋኖ ስብስብ ናቸው በማለት የኦነግ ሸኔ አባላት በማህበራዊ ድህረ ገጾች የከፈቱትን ዘመቻን የተቀበለው ወረዳውም በርካታ የሚሊሻ አባላትን ያሰረ እና ብዙዎችን አስኮርፏል። የሸኔ ቡድን ቅድመ ወረራ በስፋት የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ከፍቶ በተወሰነ መልኩ ተሳክቶለታል። መከላከያም ትጥቅ አስፈታለሁ በሚል በደራ ቱቲ ዞን ከሚያዝያ 23/2015 ጀምሮ በከፈተው ተኩስ ሰዋዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማጋጠሙ ይታወቃል። የደራ ማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና ከፍተኛ ተከታይ ያላቸው የሀገራችን አክቲቪስቶች በደራ አካባቢ እየታየ ያለው እንቅስቃሴ እጅግ አደገኛ በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ለህዝባችን ድምፅ ልትሆኑ ይገባ፤ የደራ ነዋሪዎችም ጥንቃቄ እንዳይለያቸው የሚል ጥሪ ቀርቧል። በመጨረሻም ለተሻለ የተናበበ ትግልም መከላከያ እና የደራ ወረዳ አመራሮች የአማራ ሚሊሾችን እየፈረጁ ማሰር እና ማሳደዳቸውን እንዲያቆሙ በነዋሪዎች ተጠይቋል።
Source: Link to the Post