መጀመሪያ እና መጨረሻ (አሻራ ጥር 2፣ 2013 ዓ.ም) ንጉስ ሀይለስላሴ… ይመለኩ ነበር፡፡ የምድር ፈጣሪ ሆነው አይተቹም፡፡ አይመከሩም፡፡ ስልጣናቸው የዘላለም ነው ብሎ ህዝቡ ያምናል፡፡…

መጀመሪያ እና መጨረሻ (አሻራ ጥር 2፣ 2013 ዓ.ም) ንጉስ ሀይለስላሴ… ይመለኩ ነበር፡፡ የምድር ፈጣሪ ሆነው አይተቹም፡፡ አይመከሩም፡፡ ስልጣናቸው የዘላለም ነው ብሎ ህዝቡ ያምናል፡፡ ንጉሱን መንካት ሰማይን በበሬ የማረስ ያህል ነው ብሎ ይተርታል፡፡ በሀይለስላሌ ወታደሮች አማካኝነት ጃንሆን ስልጣን ሲወርዱ ወዲያው ውሻ፣ ሽማግሌ፣ ሌባ፣ ፀረ ለውጥ፣ አቆርቋዥ፣ ዘገምተኛ፣ ጨቋኝ፣ ተብለው እየተሰደቡ ከቤተመንግስት ወደ እስር ተወረወሩ፡፡ በትራስ ታፍነውም ተገደሉ፡፡ ደርግ ሲመጣ ምድር በመስከረም አበባ ተሸልማ ነበር፡፡ ህዝቡ ፈካ፡፡ ደሃው አለፈለት ተባለ፡፡ ኮሌኔል መንግስቱ ሀይለማርያም መልኩ ጥቁር የሆነው መጪው ጊዜ የጭቁኖች እና የባሪያዎች ዘመን ስለሆነ ነው ተብሎ የምድጃ ዳር ወግ ተያዘ፡፡ ፊውዳል ይውደደም፣ ሶሻሊዝም ይፋፋም፡፡ ንጉሱ ሌባ፣ ደርግ ጥላ ከለላ እየተባለ ተዘፈነ፡፡ በንጉሱ ተበድየ ነበር እያለ ከደርግ ስልጣን መመፅዎት ፋሽን ሆነ፡፡ ንጉሱን መስደብ ፖለቲካ ሆኖ በደርግ አሾመ፡፡ ደርግን የራሱ ወታደሮች ሲከዱት እና አማፂዎች ሲረቱት የኢትዮጵያ ምድር ሁሉ ተገልብጦ ደርግ ጨቋኝ፣ አምባገነን፣ የብሄረሰቦች ጠላት፣ ህወኃት የወንዶች ቁና፣ ከወርቅ ህዝብ የተገኘ የነጠረ ጀግና እየተባለ ተሞገሰ፡፡ ደርግን መተቸት በኢህአዴግ አሾመ፡፡ ደርግነት ወንጀል ሆኖ ህወኃታዊነት ሞገስ ሆነ፡፡ በርካታ ዛሬ ላይ ያሉ የብልፅግና ካድሬዎች የልጆቻቸውን ስም በህወሃት መሪዎች ሰይመዋል፡፡ የራሳቸውን እህት አሳልፈው ለህወሃት መሪዎች የስሜት ማርኪያ አድርገዋል፡፡ አንድ ሰው ሰሩ ሲባሉ ሃያ ሰው አስረዋል፡፡ ግረፉ ሲባል ገለዋል፡፡ በህወሓት መታዘዝ በፈጣሪ እንደመታዘዝ ያለ በረከት ነው ብለው የዛሬ ብልፅግናዎች ሰርተዋል፡፡ ህወሓት አገዛዙ ሲሟሽሽ የራሱ ምልምል ቅጥረኞች ጁንታው አሉት፡፡ አምባገነን እና ፈላጭ ቆራጭ አደረጉት፡፡ ህወኃትን መስደብ የስልጣን ምንጭ ሆነ፡፡ ደርግን እና አማራን መስደብ በህወኃት ዘመን የስልጣን ምንጭ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ህወኃትን መስደብ ክብር ነው፡፡ ከእውነት አንፃር ከሆነ ፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ያስፈልጋል ያሉት እነ እስክንድር ነጋ የህወኃትም የብልፅግና እስረኛ ናቸው፡፡ ምንጊዜም በሀገራችን ስልጣን የሚጨብጡት አለቅላቂዎች እና ሚዛን አልባዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ብልፅግና እና አብይ አህመድን ህዝብ ሲፈናቀል፣ ሲገደል፣ በሀገሪቱ 4 ሚሊየን አካባቢ ሰው ለእርዳታ እጁን ሲዘረጋ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሲሽመመድ፣ ጨቋኙ ከቀድሞው ህወኃት ወደ ኦህዴድ ሲዞር ፀጥ ብሎ ውዳሴ አብይ ወ ብልፅግና ይዘረፋል፡፡ ትክክል ነገር ካልተሰራ በህወኃት የደረሰው በተረኛው ይደርሳል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህሪ ነው፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply