መፅሐፍ ተመረቀ

አርብ ሰኔ 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የራስ ብርሃን እና ሌሎች ወገኛ ታሪኮች የተሰኘውና፣ በጋዜጠኛ እና ደራሲ አሸናፊ ደምሴ የተዘጋጀ መፅሐፍ ተመርቋል።

ዛሬ ሰኔ 24 ቀን 2014 ማምሻውን በሀገር ፍቅር ቲያትር በተካሄደ መሰናዶ የተመረቀው ይህ መፅሐፍ፤ 27 አጫጭር ታሪኮችና ወጎችን ያካተተ ነው።

መፅሐፉ ከ160 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን፣ መታሰቢያነቱም ለደራሲና ወግ አዋቂው መስፍን ሀብተማርያም እንደሆነ ደራሲው በመፅሐፉ ጠቅሷል።

በምርቃት መሰናዶው ላይ ንግግር ያደረጉት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ በሥራ አጋጣሚ ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ በጋራ መሥራታቸውን አውስተው፤ <እዚህ ደረጃ እንደሚደርስ ያስታውቅ ነበር> ሲሉ መስክረዋል። የመፅሐፉን ይዘት በማድነቅም፤ ሥራው አንባብያን ዘንድ በሚገባ እንዲደርስ ደራስያን ማኅበርን ጨምሮ መገናኛ ብዙኀን እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

አያይዘውም የመፅሐፍ ህትመት ብዛት እየቀነሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወትሮ የነበረው ተቋማት መፅሐፍት እንዲገዙ ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ አውስተዋል። ይህም እንቅስቃሴ ተመልሶ ለተለያዩ ተቋማትና ለትምህርት ቤቶች የማሰራጨት ሥራ እንዲሠራ ግፊት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

በመሰናዶው ላይ በሥነፅሑፍ፣ በኪነጥበብ እንዲሁም በቴአትር የሚታወቁትና የሰንደቅ ጋዜጣ መሥራች የነበሩት ዘላለም ብርሃኑ ተገኝተዋል። ባደረጉት ንግግርም ስለደራሲና ጋዜጠኛ አሸናፊ ደምሴ ሙያዊ ብቃት እንዲሁም ምግባር አንስተው አድናቆታቸውን ሰጥተዋል።

አሸናፊ ምርቃቱን ተከትሎ ባደረገው ንግግር፤ ላገዙትና ለተባበሩት ኹሉ ምስጋናን አቅርቧል። አያይዞም “አንድ ጧፍ እልፍ ጧፎችን እንደሚያበራ ኹሉ፤ ኹሉም ሰው ድርሻውን ሊወጣና ሊያበራ ይገባል! ኹላችንም ባለን አቅም እናብራ።” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

በመድረኩ ላይ ግጥሞች፤ በመፅሐፉ ዙሪያ ዳሰሳ የቀረበ ሲሆን፤ መፅሐፉም በድምቀት በይፋ ተመርቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply