
ማኀበረ ቅዱሳን የቴሌቭዥን እገዳውን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ቦርድ የቅሬታ ደብዳቤ ላከ። የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ግንቦት 14/2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ በግንቦት 13/2015 “ሰበር ዜና” በሚል ባሰራጨው መግለጫ ምክንያት የጣቢያው ፈቃድ በጊዜያዊነት እንዲታገድ መወሰኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ማስታወቁ ይታወቃል። ጣቢያው <<ከሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ሚና ውጪ በሆነ አግባብ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያካሄደውን ስብሰባ የሚያውክና ሕዝብን ለግጭት የሚያነሳሳ መልዕክት ማሰራጨቱ ተረጋግጧል"። ያለው ባለስልጣኑ፤ ይህም የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን የሚተላለፍና በአገር ሁለንተናዊ ሰላም ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ገልጿል። በዚህም ምክንያት ከጉዳዩ አጣዳፊነትና ሊያስከትለው ከሚችለው ጉዳት አንፃር በቀጣይ በባለሥልጣኑ ቦርድ ታይቶ ዘላቂ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ የጣቢያው ፈቃድ በጊዜያዊነት የታገደ መሆኑን ገልጿል። ይህንንም ተከትሎ ማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ ለባለስልጣኑ በጻፈው የቅሬታ ደብዳቤ፤ ጣቢያው ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ለማስተማርና ወቅታዊ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን ለማሳወቅ የተቋቋመ መንፈሳዊ ጣቢያ በመሆኑ የታገደበት የፕሮግራም ይዘት ከመገናኛ ብዙኃን አዋጁ ጋር የማይጋጭ መሆኑን ዝርዝር ምክንያቶችን በማጣቀስ ገልጿል። የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንዳጋራው።
Source: Link to the Post