
ማንነትን መሠረት በማድረግና አይነኬ ሃይማኖታዊ እሴቶችን በመጣስ እየተከናወነ የሚገኘው የጅምላ ፍረጃ፣ አፈና እና እስር በአስቸኳይ ይቁም! ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ! መንግስት በማንነታቸው አማራ የሆኑ የማህበረሰብ አንቂዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ምሑራንን እና ባለሀብቶችን “ሁከት በማስነሳት፣ በሽብር ተግባርና እነዚህን መደገፍ” በሚል ጥቅል ፍረጃ እስርና አፈና በመፈጸም ላይ ተጠምዷል። በአልመከርም ባይነትም አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን በመጣስ ላይ ይገኛል። ዜጎች በያሉበት የሥራ ገበታቸው ተረጋግተው እንዳይኖሩ በማድረግ አፈናዎችን እየፈጸመ ነው። በኢትዮጵያዊያን ላይ ተስፋ መቁረጥንም አንግሷል። የብልጽግና መራሹ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አቢይ አህመድ ስልጣን በጨበጡበት ወቅት “ሳናጣራ አናስርም …” ቢሉም መንግሥታቸው ይህን ቃላቸውን ማክበር ካቃተው ሰንብቷል። አጣርቶ ማሰር ይቅርና ፍርድ ቤት በዋስ እንዲፈቱ ብይን የሰጣቸው ዜጎች ከፖሊስ ጣቢያ ሳይወጡ ፖሊስ በሌላ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ማንገላታቱ በገሃድ የታየ እውነታ ነው። እንዲህ አይነቱ የተሳከረ አካሄድ ከገጠማቸው ዜጎች አንዱ ደግሞ የእናት ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር አሰፋ አዳነ ይጠቀሳሉ። ፍርድ ቤቱ በዋስ እንዲፈቱ ወስኖ ዋስትናው የተያዘ ቢሆንም ፖሊስ በሌላ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶባቸው በእንግልት ላይ ይገኛሉ። በዋስ እንዲፈቱ ብይን የተሰጣቸው ዶ/ር አሰፋ አዳነ ዋስትናው ሊጠበቅላቸው ሲገባ ለተጨማሪ ክስ መዳረጋቸው ሆን ብሎ የማሰቃየትና የማሸማቀቅ ተግባር እንደሆነ በጽኑ እናምናለን። ይባስ ብሎም የታላቁ ቦሩ ሜዳ ጉባኤ ቤት የሐዲስ ኪዳን መምህር እና በርካታ ሊቃውንት ያፈሩትን የኔታ ኃይለማርያም ዘውዱን ከባሕር ዳር ከተማ በጸጥታ ኃይሎች ወስዶ አስሯቸዋል። እንዲህ ያለው ድርጊት ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዘመናት አስጠብቃና አጽንታ የመጣችውን የሊቃውንት አባቶችን ክብር የሚጋፋና የሚጥስ ከመሆኑ ባሻገር የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ምዕመናንንም በእጅጉ ያሳዘነ ጉዳይ ነው። መንግስት እርጋታ፣ አስተዋይነት እና ፖለቲካዊ ስክነት እርቆታል። በሁለንተናዊ ርዕይና ሀገራዊ እሳቤ እንጂ እንደ አበደ ውሻ ግራ ቀኙን ተናካሽ በመሆን የሚጸና ስልጣን እንደሌለ ግን መረዳት ያስፈልጋል። በሌላ በኩል በርካሽ ፖለቲካዊ ፍላጎትና አክራሪነት የተጠመዱ አካላት በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ አስተዳደር እና እኖር ወረዳ በሚኖሩ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች እና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ተከታታይ ግጭቶችን በመጥመቅ ላይ ይገኛሉ። በተለይም በጉንችሬ መሠናዶና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ በኸገዜ መሠናዶና ሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤት እና በጋርባዶ ሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤት በሚማሩ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍና ድብደባ ለዚህ በቂ ማሳያ ነው። የግጭቱ መነሻ የተማሪዎችን የዩኒፎርም አለባበስ ሁኔታ መነሻ ያድርግ እንጂ አፈጻጸሙ የሃይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ ፍላጎት ባላቸው አካላት የሚመራ እንደሆነ የእስካሁኑ ጉዞ ያሳያል። የሆነው ሆኖ በሃይማኖታቸው ምክንያት ተወልደው ባደጉበት ከተማ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲደርስባቸው ካለ ፍትሕ በቸልታ ማለፍ በትውልዱ ውስጥ የቂም በቀልን እንደ መዝራት ስለሚቆጠር፤ መንግስት ጉዳዩን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲፈታው ከወዲሁ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ጉዳዩ ወደ ማይበርድ ሃይማኖታዊ ግጭት እንዲያመራ በሚሰሩ ‘ግጭት ጠንሳሽ’ አካላት ላይም አፋጣኝ የእርምት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ኢትዮጵያ ሙስሊሙ እና ኦርቶዶክስ ክርስቲያኑ ለዘመናት ተከባብሮና ተዋዶ የኖረባት እና እየኖረባት ያለ ምድር ነች። በሌላው አለም የሌለ ይህን የሁለቱን ሃይማኖቶች እሴት ለማጠልሸት የሚንቀሳቀሱ አካላት በአስቸኳይ እጃቸውን ከጥፋት ሊሰበስቡ ይገባል። በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላት የጉራጌን ሕዝብ መሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች በሃይማኖት ግጭት ሸፍነው ለመሄድ እየጣሩ ያሉበት ሁኔታ ከወዲሁ ካልታረመ የማንወጣው ጦስ ውስጥ እንዳይከተንም ስጋት አለን። በሁለቱ የተከበሩ ሃይማኖቶች ላይ መቃቃር በመፍጠር ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የሚታትሩ ግለሰቦችም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ከፍትሕ አያመልጡም። ስለሆነም :- ፩. መንግስት እየተከተለ የሚገኘው ፍኖት አክሳሪ የፖለቲካ አካሄድ በመሆኑ “ጽንፈኛ” በሚል እሳቤ ማንነታቸውን (አማራነታቸውን) መሰረት አድርጎ ያሰራቸውን የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሑራን፣ ባለሀብቶች እና ሌሎች ግለሰቦችን በአስቸኳይ እንዲፈታ በድጋሜ እናሳስባለን። ፪. መንግስት አይነኬ የሆነውን ማህበረ-ባህላዊ እሴት በመጣስ በመምህር ኃይለማርያም ዘውዱ ላይ እያደረሰ ያለውን እንግልት እና እስር በአስቸኳይ አቁሞ በክብር ወደ ነበሩበት የሥራ ገበታቸው እንዲመልሳቸው እናሳስባለን። ፫. የእናት ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር አሰፋ አዳነ ፍርድ ቤት የታሰሩበትን ምክንያት ፈትሾ በዋስ እንዲፈቱ ብይን የሰጠ በመሆኑ፣ የተሰጠው “በዋስ ይፈታ ብይን” ተከብሮ ከእስር እንዲለቀቁ እንዲያደርግልን እንጠይቃለን። ፬. መንግሥት በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ እና አጎራባች ቀበሌዎች እንዲሁም በእኖር ወረዳ በሚገኙ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች እና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ያለውን መልካም ትስስር ለማጠልሸት እየሰሩ የሚገኙ አካላትን በመለየት በአስቸኳይ ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያመጣ እንጠይቃለን። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይጠብቅ! እናት ፓርቲ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ግንቦት ፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post