#ማይግሬን (MIGRAINE)ማይግሬን በአለም ዙሪያ በጣም ከተለመዱ በሽታዎች አንዱ ነው፡፡በአለም ላይ ከ148 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በዚህ ህመም የተጠቁ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡እንዲሁም…

#ማይግሬን (MIGRAINE)

ማይግሬን በአለም ዙሪያ በጣም ከተለመዱ በሽታዎች አንዱ ነው፡፡

በአለም ላይ ከ148 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በዚህ ህመም የተጠቁ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

እንዲሁም ከ 10 % በላይ የሚገመቱ ሰዎች በዚህ ህመም ይጎዳሉ፡፡

ብዙ ግዜ የሚከሰተው ከ20 እስከ 50 አመት እድሜ ውስጥ ያሉ ሰዎች ላይ መሆኑም ይነገራል፡፡

የማይግሬን ህመም በሴቶች ላይ ከወንዶች ይልቅ በ3 እጥፍ የመከሰት እድል እንዳለው ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡

በዚህ ጉዳይም ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን ከአንገት በላይ ህክምና ስፔሻሊስት እና የመስማት ችግሮች ህክምና ልዩ ስፔሻሊስት ዶ/ር ሚካኤል ከበደ ጋር ጣቢያችን ቆይታ አድርጓል፡፡

#ማይግሬን (MIGRAINE) ምንድን ነው ?

ማይግሬን ከፍተኛ ሆነ የራስ ምታት ችግር ነው ይላሉ፡፡

ቀዳሚ የሆነ የራስ ህመም ሲሆን ከፍተኛ ህመም የሚያመጣ የሰውነት ችግር ነው፡፡

#መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው?

የማይግሬን ህመም በሽታ እስካሁን መንስኤው ተጣርቶ እንደማይታወቅ ይናገራሉ፡፡

ግን ጥናቶች እንደሚያሳዩት በብዛት ሴቶች ላይ የሚታው በተለይ ከ30 አመት በላይ ያሉ ሴቶች ላይ የመብዛት ባህሪ እንደሚታይበት ይናገራሉ፡፡

ማይግሬን ዋናው መገለጫው ከፍተኛ የሆነ የራስ ምታት ነው ፡፡

ብዙ ሰዎች ላይ በግማሽ ከፍሎ የሚያማቸው ሲሆን አንድ አንድ ሰዎች ላይ ደግሞ ሙሉ ጭንቅላታቸውን ወጥሮ መያዝ ስሜት ሊኖረው ይችላል ፡፡

የማግሬን ህመም ያለባቸው ሰዎች ህመሙ ሊነሳባቸው ሲል የሚሰሟቸው ስሜቶች ሊኖሩ ይችላል ከነዛም መካከል
– ደማቅ ብርሀን መታየት
– ድምፅ መሰማት
– የሆነ አይነት ሽታ ሊሸታቸው ይችላል
– የጭንቀት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል፡፡

አንዳንድ ግዜ ደግሞ ያለምንም ስሜት ሊከሰት ይችላል፡፡

#የማይግሬን ህመም ሊያስነሱ የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ወደ ጭንቅላታችን የሚሄደው የደም ዝውውር ላይ ተፅዕኖ ሲኖር ነው ተብሎ ይታሰባል ይላሉ፡፡

ማይግሬን ያለባቸው ሰዎች ልክ ማይግሬናቸው ሲነሳ ወደ ጭንቅላታቸው ሚፈሰው የደም ዝውውር በጣም ይጨምራል፡፡

ሴቶች ላይ ደግሞ ሚበዛበት ምክንያት የወር አበባን ከሚቆጣጠር ሆርሞኖች ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችል ነው፡፡

የማይግሬን ችግር ሲከሰት በትንሹ ለ3 ሰአት ሊቆይ የሚችል እና ከፍ ካለም 3 ቀን እና ከዛ በላይ ሊቆይ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

#የሚታዮ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

– ስራ ለመስራት መቸገር
– ነገሮች ላይ ትኩረት ለማድረግ መቸገር
– የምግብ አለመስማማት
– ማቅለሽለሽ እና ወደላይ ማለት ይጠቀሱበታል፡፡

ከሌሎች እራስ ምታቶች ማይግሬንን ለየት የሚያደርገው ከፍተኛ የሆነ ብርሀን እንዲሁም ጫጫታ እና ድምጽ በቀላሉ ይረብሻቸዋል።

ስለዚህ ህመሙ ሲነሳባቸው ጨለም ያለ እና ፀጥ ያለ ክፍል ውስጥ መተኛትን ይመርጣሉ፡፡

በብዙ ሰው ላይ ችግሩ ሊባባስ የሚችለው ሲናደዱ እና ሲጨናነቁ እንደሆነ የነገሩን ባለሙያው ህመሙ ሲከሰት እነዚህን ነገሮች ማስወገድ እንደሚጠቅም አንስተዋል፡፡

ለማይግሬን ዋናው አጋላጭ ናቸው ተብለው ከሚታሰቡ ነገሮች አንዱ በቤተሰብ አንድ ሰው ህመሙ ካለበት የመከሰት እድል እደሚኖረው ባለሙያው አንስተዋል፡፡

#ለመከላከል ምን መደረግ አለበት?

– ጭንቀት ማስወገድ
– በቂ እንቅልፍ እንዲያገኙ ማድረግ እና በለመዱት ሰአት መተኛት እና መነሳት
– የእንቅልፍ ሰአታቸው ሲደርስ የሚያነቃቁ ነገሮችን መውሰድ አይመከርም ( ቡና)
– ለማይግሬን ተብለው የሚታዘዙ መድሃኒቶችን ተመርምሮ በደረጃው ልክ መድሀኒት መውሰድ

በመጨረሻም ማይግሬን የተለመደ ችግር እና አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል እንደሚያጠቃ ጥናቶች ስለሚያሳዮ ይህ ችግር የሚያጋጥማቸው ሰዎች የአንድ ግዜ ብቻ ህክምና ስላልሆነ የሚያስፈልጋቸው የነርቭ ስፔሻሊስት ሀኪሞች ጋር በመሄድ ተገቢውን ህክምና ማግኘት እንዳለባቸው ዶ/ር ሚካኤል ተናግረዋል፡፡

#በሐመረ ፍሬው
ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply