ማይፀብሪ ላይ በአየር ጥቃት የ17 ሰው ህይወት መጥፋቱ ተነግሯል

ትግራይ ውስጥ ማይፀብሪ ከተማ ላይ ተፈፅሟል በተባለ የአየር ጥቃት ቢያንስ 17 ሰዎች መገደላቸውንና ብዙዎች መቁሰላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የዜና አውታሩ በዘገባው ከሞቱት አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸውን የረድዔት ሠራተኞችንና የአካባቢውን ባለሥልጣናት እንደነገሩት አመልክቷል።

ባለፈው ዓርብም መካሄዱ በተነገረ ሌላ ድብደባ መጠለያ ሠፈር ውስጥ የነበሩ ህፃናትን ጨምሮ የ56 ሰዎች ህይወት መጥፋቱና ሌሎች 30 ሰዎች መቁሰላቸው መዘገቡን ሮይተርስ አክሎ አስታውሷል።

ህወሓት ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲቪሎች ላይ ጥቃት ይፈፅማል ሲል ከስሷል።

ስለጥቃቱ ክሥ ምላሽ እንዲሰጡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነንና የመንግሥቱን ቃል አቀባይ ዶ/ር ለገሰ ቱሉን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን ሮይተርስ ገልጿል።  

የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል ተፈፅሟል ለተባለው ተመሳሳይ ጥቃት በሰጠው ምላሽ ሰላማዊ ሰዎችን ላይ ጥቃት እንደማያደርስ ማስታወቁንም ሮይተርስ ጠቁሟል። 

በሌላም በኩል አስራ አራት ወራትን በፈጀው እና እስካሁንም በዘለቀው ጦርነት ከሰሞኑ በስደተኞች መጠለያዎች ላይ ከባድ የአየር ጥቃት መድረሱን ተከትሎ በትግራይ ክልል ውስጥ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የረድኤት ተቋማት ሥራ ለማቋረጥ መገደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ አገልግሎቶች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤንኦቻ) ከትናንት በስተያ ዕሁድ ማስታወቁ ተዘግቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply