ሜላትወርቅ ኃይሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በሰብሳቢነት እንዲመሩ ተሾሙ 

በተስፋለም ወልደየስ

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤትን በኃላፊነት የመሩት ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ አምስት አባላት ያሉበትን የምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ በሰብሳቢነት እንዲመሩ በዛሬው ዕለት ተሹመዋል። የቦርዱ ሰብሳቢ ሹመታቸው በፓርላማ የጸደቀላቸው በአንድ ጽምጸ ተዐቅቦ ነው።

ምርጫ ቦርድን ለአራት ዓመት ከመንፈቅ በሰብሳቢነት የመሩት ብርቱካን ሚደቅሳን የተኩት ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ከ30 ዓመት  በላይ ሀገራቸውን በተለያዩ የስራ መስኮች ያገለገሉ መሆናቸው በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ላይ ተገልጿል። ተሿሚዋ በሙያቸው ካገለገሉባቸው ተቋማት መካከል መንግስታዊው የጉሙሩክ ባለስልጣን እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሆነው ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርስቲ ይጠቀሳሉ።

ሜላትወርቅ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን በነበራቸው የአስር ዓመታት ቆይታ፤ የመስሪያ ቤቱን የኦፕሬሽን መምሪያ እንዲሁም የህግ አፈጻጸም መምሪያን በኃላፊነት እስከ መምራት ተጉዘዋል። ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በተቋቋመበት ወቅት፤ የተለያዩ የትምህርት መስኮችን ስርዓተ ትምህርት ቀረጻ የመምራት ሚና መጫወታቸው እና የዩኒቨርስቲ ኮሌጁ የሴኔት አባል ሆነው ማገልገላቸው ተነግሯል።

አዲሷ ተሿሚ በግላቸው ባቋቋሙት ድርጅት የህግ ማማከር እና ስልጠና፤ የህግ ሰነዶች ዝግጅት፣ የድርድር እና የግልግል አገልግሎትን ለደንበኞቻቸው ሲሰጡ መቆየታቸውም በስራ ልምድ ዝርዝራቸው ላይ ተጠቅሷል። ሜላትወርቅ በዚሁ ድርጅታቸው አማካኝነት፤ ለሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች የስትራቴጂ እና የፖሊሲ ሰነዶችን የመቅረጽ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበርም ተመላክቷል። 

ሜላትወርቅ ዛሬ በቦርድ ሰብሳቢነት እንዲመሩት የተሾሙበትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በጽህፈት ቤት ኃላፊነት የተቀላቀሉት፤ መስሪያ ቤቱ ሀገር አቀፍ ምርጫን ከማካሄዱ ከአንድ አመት በፊት ነበር። የተሿሚዋን ዝርዝር የስራ ልምድ እና የትምህርት ዝግጅት ለፓርላማ አባላት ያቀረቡት በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ ሜላትወርቅ በዚሁ ኃላፊነታቸው ወቅት “ከመላው ሰራተኛ እና የቦርድ አመራር ጋር በመሆን ምርጫ 2013 እንዲሁም በክልሎች የተካሄዱ ህዝበ ውሳኔዎችን በብቃት የመሩ [ናቸው]” ብለዋል።  

“በአጠቃላይ በምርጫ ቦርድ የሪፎርም ስራዎች በብቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ፤ እስካሁን በተመደቡበት በታማኝነት በትጋት እና በቅንነት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ የቆዩ ናቸው” ሲሉም አቶ ተስፋዬ የምርጫ ቦርድን አዲሷን የቦርድ ሰብሳቢ አሞካሽተዋቸዋል። ሜላትወርቅ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ቦርድ አባል ያለመሆናቸውን የጠቀሱት የመንግስት ተጠሪው፤ ባላቸው “ሰፊ ልምድ” “የምርጫ ቦርድን ስራ በወጤታማነት ይመራሉ ተብሎ እምነት የተጣለባቸው በመሆኑ” ፓርላማው ሹመታቸውን እንዲያጸድቅ ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Source: Link to the Post

Leave a Reply