You are currently viewing ምርጫ ቦርድ በሁለት ጎራ በተከፈሉት የኦነግ አመራሮች ላይ ውሳኔ ሊሰጥ ነው

ምርጫ ቦርድ በሁለት ጎራ በተከፈሉት የኦነግ አመራሮች ላይ ውሳኔ ሊሰጥ ነው

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በሁለት ጎራ የተከፈሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች አለን የሚሉትን ክርክር እና ማስረጃ በሶስት ሳምንት ጊዜ ለቦርዱ እንዲያቀርቡ አሳሰበ። ምርጫ ቦርድ ማሳሰቢያውን የሰጠው፤ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ፍርድ መሰረት የሁለቱንም ወገኖች ክርክር በድጋሚ ሰምቶ ውሳኔ ለማሳለፍ ነው።

የኦነግ አመራሮች፤ በምርጫ ቦርድ ዘንድ በሊቀመንበርነት በሚታወቁት በአቶ ዳውድ ኢብሳ እና በምክትላቸው አቶ አራርሶ ቢቂላ በሚመሩ ሁለት ቡድኖች ተከፍለው መወዛገብ የጀመሩት ከነሐሴ 2012 ጀምሮ ነው። በእነ አቶ አራርሶ የሚመራው የግንባሩ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ በፓርቲው ሊቀመንበር ላይ የእግድ ውሳኔ ከማስተላለፍ አንስቶ ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ በማድረግ ለውጦቹ እንዲጸድቁለት ለምርጫ ቦርድ አስታውቆ ነበር።  

በአቶ ዳውድ የሚመራው የኦነግ ቡድን በበኩሉ አቶ አራርሶ ቢቂላን ጨምሮ አምስት የግንባሩ አመራሮች ከፓርቲው መታገዳቸውን በመግለጽ ቦርዱ ውሳኔውን እንዲያጸድቀው ጥያቄ አቅርቧል። የሁለቱን ቡድኖች ማመልከቻዎች ሲመረምር የቆየው ምርጫ ቦርድ በመጋቢት 2013 ባሳለፈው ውሳኔ፤ በአቶ አራርሶ የሚመራው ኦነግ ያከናወነው “ጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት የለውም” ሲል ውድቅ አድርጎታል። ቦርዱ፤ ፓርቲውን የመምራት ህጋዊ ስልጣን ያላቸው አቶ ዳውድ እንደሆኑ እና አቶ አራርሶም በምክትል ሊቀመንበርነታቸው እንደሚቀጥሉ በወቅቱ አስታውቆ ነበር። 

በቦርዱ ውሳኔ ቅር የተሰኘው በአቶ አራርሶ የሚመራው የኦነግ ቡድን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ክርክር ሲያደርግ ቆይቷል። ከከፍተኛ ፍርድ ቤት እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ክርክር የተደረገበት የኦነግ ጉዳይ በስተመጨረሻ በሰበር ሰሚ ችሎት የፍርድ ውሳኔ ተጠናቅቋል። የሰበር ሰሚ ችሎቱ ያስተላለፈው የፍርድ ውሳኔ፤ ምርጫ ቦርድ “የሁለቱንም ወገኖች ክርክር እንደገና ሰምቶ ውሳኔ ይስጥ” የሚል ነበር።

ምርጫ ቦርድ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ለጠየቀው ተጨማሪ ማብራሪያ፤ በጥቅምት ወር ምላሽ ማግኘቱን ለሁለቱም ወገኖች በላከው ደብዳቤ አስታውቋል። ቦርዱ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ህዳር 29፤ 2014 በላከው በዚሁ ደብዳቤ፤ ሁለቱም ወገኖች ደብዳቤው ከደረሳቸው ቀን ጀምሮ ባሉት ሶስት ሳምንታት “አለን የሚሉትን ክርክር እና ማስረጃ እንዲያቀርቡ” አዝዟል። 

ሁለቱ የኦነግ ቡድኖች ክርክራቸውን እና ማስረጃዎቻቸውን እንዲያቀርቡ የታዘዙት በሶስት ጭብጦች ላይ ነው። የመጀመሪያው ጭብጥ በእነ አቶ አራርሶ አማካኝነት መጋቢት 4፤ 2013 የተጠራው ጠቅላላ ጉባኤ “በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ተጠርቷል ወይስ አልተጠራም?” በሚለው ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው። 

አመራሮቹ ማስረጃ እንዲያቀርቡበት የተጠየቁት ሁለተኛው ጭብጥ ደግሞ ጠቅላላ ጉባኤው በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የተጠራ ከሆነ፤ ጉባኤው የሰጠው ውሳኔ እና ለቦርዱ የቀረበው ቃለ ጉባኤ የፓርቲው “ደንቡ በሚያስቀምጠው መሰረት የተሰራ ነው ወይስ አይደለም?” የሚለውን የሚመለከት ነው። ቦርዱ ማስረጃ እንዲቀርብበት የጠየቀው ሶስተኛው ጭብጥ፤ እነ አቶ አራርሶ ለቦርዱ ያቀረቧቸው ሰነዶች “የተሟሉ ናቸው ወይስ አይደሉም?” የሚለው ነው። 

በእነ አቶ ዳውድ የሚመራው የኦነግ ቡድን ምላሽ ለማዘጋጀት ይረዳው ዘንድ፤ በጉዳዩ ላይ በፍርድ ቤት የተደረጉ ክርክሮች እና በየደረጃው የተሰጡ ውሳኔዎች ግልባጭ እንዲደርሱት መደረጉን ቦርዱ አስታውቋል። ምርጫ ቦርድ የፍርድ ቤት ክርክሮችን ሲያደርግ የቆየው በአቶ አራርሶ ከሚመራው ቡድን ጋር ብቻ ነበር።

የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ቦርዱ የሁለቱም ወገኖች ምላሽ ከደረሰው በኋላ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ያስተላልፋል። “ቦርዱ ከሁለቱም አካላት የቀረቡትን ምላሾች አይቶ፤ በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት በጉዳዩ ላይ አስፈላጊ ነው የሚለውን ውሳኔ ይሰጣል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

The post ምርጫ ቦርድ በሁለት ጎራ በተከፈሉት የኦነግ አመራሮች ላይ ውሳኔ ሊሰጥ ነው appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply