በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የተደረገው ህዝበ ውሳኔ እና የመራጮች ምዝገባ ውድቅ ተደርጎ በድጋሚ እንዲካሄድ ወሰነ፡፡ ቦርዱ በዞኑ የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ውድቅ ያደረገው፤ “መጠነ ሰፊ” ጥሰቶች በመፈጸማቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው፤ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ህዝበ ውሳኔን አስመልክቶ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 22፤ 2015 በሰጠው መግለጫ ነው፡፡ በዚሁ መግለጫ ላይ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፤ አጠቃላይ የህዝበ ውሳኔውን ሂደት እና በወላይታ ዞን የነበረውን ጥሰት በተመለከተ የተሰጠውን ውሳኔ በንባብ አሰምተዋል።
ቦርዱ በዛሬ መግለጫው በወላይታ ዞን የተፈጸመው ጥሰት “የምርጫ ሂደቱን ተዓማኒነት እና እውነተኝነት ያሳጣ እና አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱንም የሚያዛባ” መሆኑን ገልጿል። አቶ ውብሸት “የወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ውድቅ እንዲደረግ እና የመራጮች ምዝገባ እና ድምጽ አሰጣጡም በድጋሚ እንዲደረግ ቦርዱ ወስኗል” ሲሉ የወላይታ ዞን የህዝበ ውሳኔ ሂደትን በተመለከተ የቦርዱን ውሳኔ ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ “ጥሰቶቹን ያስፈጸሙ፣ የፈጸሙ እና የተባበሩ” ያላቸውን አካላት በመለየት ምርመራ እንዲያከናውን እና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት እንዲያደርግ ለፌደራል ፖሊስ ደብዳቤ እንዲጻፍ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
The post ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የተደረገው ህዝበ ውሳኔ በድጋሚ እንዲካሄድ ወሰነ appeared first on Ethiopia Insider.
Source: Link to the Post