ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል በሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ዙሪያ የመራጮች ትምህርት መሰጠት ለሚፈልጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥሪ አቀረበ

ዕረቡ ጥቅምት 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ስር የሚገኙ 6 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች በሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ዙሪያ የመራጮች ትምህርት መሰጠት ለሚፈልጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥሪ አቀረበ።

“ዜጎች ህዝበ ውሳኔው ላይ ያላቸውን ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማረጋጋጥ ብሎም ተአማኒነትን ያተረፈ ሰላማዊ ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ የመራጮች ትምህርት አስፈላጊነት እሙን ነው፡፡” ያለው ቦርዱ፤ ይህንን አላማ ለማሳካትም የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎ ትልቅ ሥፍራ እንደሚይዝ ገልጿል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቦርዱን ባቋቋመው አዋጅ ቁጥር 1133/2011 እንዲሁም የመራጮች ትምህርት ፈቃድ አሰጣጥ እና የሥነ ምግባር መመሪያ ቁጥር 04/2012 መሰረት፤ በህዝበ ውሳኔው ሂደት የመራጮች ትምህርት መስጠት ለሚፈልጉ እና ትምህርቱን ለመስጠት ብቃት ላላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ሠጥቶ ማሰማራት አስፈላጊ ሆኖ ማግኘቱን አስታውቋል።

በዚህ መሠረት፤ በህግ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ፣ የማስተማሩን ተግባር ለመወጣት የሚያስችል ብቃት ያላቸው፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ገለልተኛ የሆኑ እንዲሁም በተለያየ ዘዴ የመራጮች ትምህርት ለመስጠት የሚፈልጉ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለመራጮች ትምህርት መሰጠት እንደሚችሉ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።

በመሆኑም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ለዚህ የተዘጋጀ ማመልከቻ በመሙላት አግባብነት ካለቸው ሰነዶች (ማለትም የምዝገባ ሰርተፊኬት ቅጂ፣ ለአሰተባባሪዎችና አሰልጣኞች አባሪ ቅጽ፣ የስልጠና እቅድ እና ለሥራ የሚያስፈልግ በጀት…) ጋር በማያያዝ፤ በኢሜል አድራሻ [email protected] እንዲልኩ ወይም በዋናው መ/ቤት ቢሮ ቁጥር 102/106 እንዲሁም ለቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ከዛሬ ጥቅምት 16 ቀን ጀምሮ በ10 ቀናት ውስጥ በኣካል እንዲያቀርቡ ቦርዱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ከዚህ በፊት የማስተማር ፈቃድ ጥያቄ ያቀረቡ ማህበራትም ለእነርሱ በተለይ የተዘጋጀውን ማመልከቻ በመሙላት ሊያቀርቡ እንደሚገባም ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ስር የሚገኙ 6 ዞኖች ማለትም የጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዲዮ፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች ማለትም የቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌ ልዩ ልዩ ወረዳዎች ጥር 29 ቀን 2015 ህዝበ ውሳኔውን እንደሚያካሄድ ማስታወቁ ይታወሳል።

The post ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል በሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ዙሪያ የመራጮች ትምህርት መሰጠት ለሚፈልጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥሪ አቀረበ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply