ምርጫ ቦርድ ባልደራስ መስከረም 29 ቀን 2015 አካሂደዋለሁ ያለውን ጠቅላላ ጉባዔ ውድቅ ማድረጉን አስታወቀ

አርብ መስከረም 20 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ መስከረም 29 ቀን 2015 አካሂደዋለሁ ያለውን ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ ያስገባውን ሠነድ መርምሮ ሕጉንና የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ የተከተለ ሆኖ ስላላገኘው ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል።

ቦርዱ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ነሐሴ 21 ቀን 2014 በቁጥር ባ/ለ/ዲ00552 በተፃፈና የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት በሚል በተፈረመ ደብዳቤ፤ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ነሐሴ 15 ቀን 2014 መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ያልተሟሉ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን ማሟላቱን እንዲሁም፤ ነሐሴ 23 ቀን 2014 በቁጥር ባ/ለ/ዲ/00566 በተፃፈ ደብዳቤ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት መስከረም 29 ቀን 2015 ጠቅላላ ጉባኤ እንዲደረግ መወሰኑን አሳውቆኛል ብሏል።

ቦርዱ መስከረም 12 ቀን 2015 ባካሄደው ስብሰባ የቀረበውን ሰነድ መመርመሩን የገለጸ ሲሆን፤ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አቀፅ 14.1 ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት እስከ 45 ቋሚ እና 15 ተለዋዋጭ አባላት እንደሚኖሩት፤ በአንቀፅ 14.2 ንዑስ አንቀፅ2 ብሔራዊ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤውን መደበኛ፣ ልዩና አስቸኳይ ስብሰባዎች እንደሚጠራ፣ በአንቀፅ 19.7 ንዑስ አንቀፅ 1 በማንኛውም ፓርቲው ስብሰባ ላይ ከግማሽ በላይ ሆኑ አባላት ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ እንደተሟላ እንደሚቆጠር፤ በንዑስ አንቀፅ 2 ደግሞ ምልዓተ ጉባኤው ለኹለት ተከታታይ ጊዜ ካልተሟላ ሦስተኛው ተጠርቶ በተገኙት አባላት እንደሚካሄድ መደንገጉን ገልጿል።

ይሁንና ብሔራዊ ምክር ቤቱ በነሐሴ 15 ቀን 2014 ተሰብስቦ ሥራ አስፈፃሚ አባላትን ማፅደቁ እና ጠቅላላ ጉባኤ ቀን ወስኗል በሚል በቀረበው ቃለ ጉባኤ 12 አባላት እንደተሰበሰቡ፤ ይህም የሆነው ኹለት ጊዜ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ስብሰባ ተጠርቶ ምልዓተ ጉባኤ ባለሟላቱ ምክንያት እንደሆነ በመግለፅ ስብሰባውን እንደቀጠሉ ተገልጿል።

በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል ከተባሉትና ቦርዱ እውቅና ከተሰጣቸው 45 ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት መካከል የተገኙት 7 ብቻ መሆናቸውን ይሁንና የቀረበው ሰነድ ብሔራዊ ምክር ቤቱ በደንቡ አንቀፅ19.2.2 መሰረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በወሰነው ቦታና ጊዜ ኹለት ጊዜ ተጠርቶ እንደነበር እና ምልዓተ ጉባኤውም በኹለቱ የተጠሩ ስብሰባዎች ያልተሟላ የነበረ ስለመሆኑ አያሳይም ሲል ምርጫ ቦርድ ገልጿል።

በዚሁ መሠረት በነሐሴ 15 ቀን 2014 ብሔራዊ ምክር ቤቱ አካሂዶታል የተባለው ስብሰባ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል።

በዕለቱ የመጀሪያው አጀንዳ የነበረው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን ማፅደቅ ሲሆን፤ በመተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 16.1 እ5 20.1.10 ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ቀርቦ ከመፅደቁ በፊት በፕሬዚዳንቱ መመረጥ እንዳለባቸው ይደነግጋል ያለው ቦርዱ፤ ነገር ግን የፓርቲው ፕሬዚዳንት የመረጧቸው ሥራ አስፈፃሚዎች የፀደቁ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማረጋገጫ/ማስረጃ ያልቀረበ በመሆኑ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የተባለው ውሳኔ ተቀባይነት አለማግኘቱን ገልጿል።

ኹለተኛው አጀንዳ የጠቅላላ ጉባኤ ቀን መወሰንን በተመለከተ ሲሆን፤ በ12 የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ተደረገ የተባለው ስብሰባ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ተከትሎ የተካሄደ ባለሆኑ መስከረም 29 ቀን 2015 ጠቅላላ ጉባኤ እንዲደረግ የተላለፈው ውሣኔም ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፡፡

ስለሆነም፤ ቦርዱ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በነሐሴ 15 ቀን 2014 ተሰብስቦ አሳልፏቸዋል የተባሉትን ውሣኔዎች ያልተቀበላቸው መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ፓርቲው በመስከረም 29 ቀን 2015 ለማድረግ ያቀደው ጠቅላላ ጉባኤም ተቀባይነት የሌለው በሆኑ ታዛቢ እንደማይልክ መወሰኑን አስታውቋል።

The post ምርጫ ቦርድ ባልደራስ መስከረም 29 ቀን 2015 አካሂደዋለሁ ያለውን ጠቅላላ ጉባዔ ውድቅ ማድረጉን አስታወቀ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply