You are currently viewing ምርጫ ቦርድ ከአብን ጠቅላላ ጉባኤ ጋር በተያያዘ ከ300 በላይ የሚሆኑ የጉባኤ አባላትን ፊርማ በማካተት በቀረበለት አቤቱታ ላይ ውሣኔ እንደሚሰጥበት አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ…

ምርጫ ቦርድ ከአብን ጠቅላላ ጉባኤ ጋር በተያያዘ ከ300 በላይ የሚሆኑ የጉባኤ አባላትን ፊርማ በማካተት በቀረበለት አቤቱታ ላይ ውሣኔ እንደሚሰጥበት አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ…

ምርጫ ቦርድ ከአብን ጠቅላላ ጉባኤ ጋር በተያያዘ ከ300 በላይ የሚሆኑ የጉባኤ አባላትን ፊርማ በማካተት በቀረበለት አቤቱታ ላይ ውሣኔ እንደሚሰጥበት አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ሚያዝያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ተወካይ ኮሚቴ የተሰጠው መግለጫ የሚከተለው ነው:_ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔ መጥራቱ ይታወሳል። በጉባኤው አጠቃላይ ሦስት አጀንዳዎች ተይዘው ሁለቱ የተቋጩ ሲሆን ሦስተኛው ማለትም ሪፎርምን የተመለከተው አጀንዳ በሰብሳቢዎች መድረክ ረግጦ መውጣት ምክንያት አጀንዳው ሳይጠቃለል ጉባዔው መበተኑ ይታወቃል። ለዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች መታዘባቸው፣ የተጠናቀቀና በጉባዔተኛው የተፈረመበት የጉባዔ ቃለጉባዔ አለመኖሩ እና ከሦስት መቶ በላይ ጉባኤተኛ በፊርማ አስደግፎ ያቀረበው አቤቱታ ማሳያወች ናቸው። ይህን በተመለከተም የጠቅላላ ጉባዔው አባላትን የቅሬታ ፊርማ በማሰባሰብ በአስቸኳይ ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ድጋሚ ጉባዔ ተጠርቶ ያልተጠናቀቀው አጀንዳና ጉባዔው እንዲጠናቀቅ መጋቢት 19 ቀን 2014 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ መጠየቃችን ይታወቃል። ይህንንም ደብዳቤ በግልባጭ ለፓርቲው ማዕከላዊ ጽ/ቤት እና ለኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ማሳወቃችን የሚታወስ ነው። እንደገና መጋቢት 26 ቀን 2014 ዓ.ም ለአቤቱታችን በፅሁፍ ምላሽ ይሰጠን ስንል ቦርዱን ጠይቀናል። ለዚህ ጥያቄያችን ቦርዱ ሚያዝያ 04 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥር አ1162/11/587 በተፃፈ ደብዳቤ ከ300 በላይ በሆነ የጉባኤው አባላት ፊርማ አስደግፈን ያቀረብነውን አቤቱታ ጠቅላላ ጉባኤውን የታዘቡት የቦርዱ ተወካዮች ያቀረቡትን ሪፖርት እና የፓርቲው አመራር ጠቅላላ ጉባዔውን አስመልክቶ ካቀረበው ሪፖርትና ሰነዶች ጋር በመመርመር ቦርዱ ውሣኔ የሚሰጥበት መሆኑን አሳውቆናል። ከዚህም በተጨማሪ የዳግም ጉባዔና የሪፎርም እንቅስቃሴን አመራሩ መደገፍ እንዳለበት የሚገልጽ ደብዳቤ ሚያዝያ 06 ቀን 2014 ለፓርቲው ማዕከላዊ ጽ/ቤት ማስገባታችንን ማሳወቅ እንፈልጋለን። በ3ኛው የድርጅታችን ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተሳተፈው የጉባዔው አባል ከፍተኛ የሆነ የመርኅ ትግል በማድረግ በአገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴና ጠቅላላ ጉባዔ ታሪክ ውስጥ ልዩ አሻራን አሳርፏል፤ ለዚህም ልዩ ክብር ይገባዋል። ሆኖም ግን ለአማራ ሕዝብ ይህ የጉባዔ አባል ማሳየት ያለበት አዲስ ታሪክ መጀመርን ብቻ ሳይሆን አዲስ ታሪክ ሰርቶ መፈፀምን ጭምር መሆን አለበት። በመሆኑም ይህ ጉባዔው የጀመረውን ታሪክ የመስራት ሂደት ለእነዚህና ከዚህም ከፍ ብለው ሊመጡ ለሚችሉ ፈተናዎች ሳይበገር የተነሳለትን አጠቃላይ ድርጅታዊ ዓላማዎች ግብ ላይ በማድረስ የሕዝባችን ተስፋና የቀጣይ ትውልድ የመልካም ታሪክ ተጠቃሽ እንዲሆን ከትልቅ ታሪካዊ አደራ ጋር የተናበበና ንቁ እንቅሰቃሴ ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አበክረን ማሳሰብ እንወዳለን። ይህን ለአማራ ሕዝብ ትግል መጠናከር እና ለኢትዮጵያ ችግሮች መፈታት ትልቅ ተስፋ ሰጭ የሆነን የጉባዔው ሂደትና የሪፎርም ጥያቄ በማሰልቸት፣ ለመከፋፈል በመሞከር፣ በማወናበድ፣ ተተኪ ብቁ አመራር የሌለ በማስመሰል፣ ጫና በማድረግ፣ ተገቢ ባልሆነ ሽምግልና በመማፀን፣ በማስፈራራትና በመሰል ፈተናዎች በፍፁም የሚገታ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ከጉባዔው ጥያቄ ጋር በተያያዘ ያለውን ቀጣይ ሂደትና ውጤት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ የምናሳውቅ ሲሆን ከዚህ አያይዘን የሚከተሉትን መልዕክቶች ማስተላለፍ እንፈልጋለን:_ 1ኛ) ለፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮች ጠቅላላ ጉባዔው የማዕከላዊ ኮሚቴ እና የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ለውጥ (ሪፎርም) ያስፈልጋል ብሎ በፅኑ ሲጠይቅና ሲሞግት የራሱ የሆኑ ድርጅታችንን በጠንካራ አቋም ላይ ከማስቀመጥና የአማራን ሕዝብ ሁለንተናዊ ትግል ከማስተካከል አንፃር የተቃኙ አሳማኝ ምክንያቶች አሉት። ሆኖም ግን ይህን ጥያቄ ላለመቀበል በጉባዔው ዕለት የነበረው የአባላትን ድምፅና ኃሳብ ማፈን፣ መብት ድፍጠጣና የመርኅ ጥሰት የድርጅታችንን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ብሎም የአማራን ሕዝብ ክብር የሚነካና ተገቢ ያልሆነ ድርጊት መሆኑን ማስታወስ እንወዳለን። ከዚህም በተጨማሪ ከጉባዔው በኋላ በፓርቲያችን የፌስ ቡክ ገፅ ስለ ጉባዔው ከተሰጠው መግለጫ ጀምሮ እስከ አመራሮች ቃለ ምልልስ የታዩ ተገቢነት የሌላቸው የተሳሳቱ፣ እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ እንዲሁም ለአባሉና ለሕዝቡ የማይመጥኑ መሆናቸውን እያስታወስን አመራሮች ከመሰል የራሳቸውን የወደፊት የፖለቲካ ተሳትፎና ድርጅቱንም ከሚጎዱ እንቅስቃሴዎች እንዲታቀቡ አበክረን እያሳሰብን ጠቅላላ ጉባዔው በግልፅ ያቀረበውን የሪፎርም ጥያቄ በቀናነት ማየት እንዲጀምርና የጠቅላላ ጉባዔውን ጥያቄ ብቻ መሰረት ባደረገ መልኩ የሪፎርም ጥያቄው መመለስ እንዳለበት እናሳስባለን። 2ኛ) ለፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ድርጅታችን አሁን ለታየበት ድክመት ዋና ተጠያቂ ከሆኑት አካላት ውስጥ አንዱ የማዕከላዊ ኮሚቴው መሆኑ ይታወቃል። አሁን በድርጅቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ የድርጅቱን እንዲሁም በዛሬውና በወደፊቱ የአማራ ሕዝብ ትግል እና በአጠቃላይ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚያሳርፈው አውንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑ እሙን ነው። በመሆኑም ሁሉም የኮሚቴው አባላት ለድርጅቱና ለአማራ ሕዝብ በመታመን ከግለሰባዊ ፍላጎትና ከታሪክ ተወቃሽነት ነፃ የሚያደርግ መልካም አሻራ እንዲያስቀምጥ አጥብቀን እናሳስባለን። ከድጋሚ ጉባዔውና ከሪፎርሙ ጋር በተያያዘ ጠቅላላ ጉባዔው የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ጠንክረው እንዲደግፉና ጉዳዩ የጠቅላላ ጉባዔውን አቅጣጫ መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲፈታ አበክረን እናሳስባለን። 3ኛ) ለድርጅታችን አባላት፣ ለደጋፊዎች፣ ለአማራ ሕዝብና ለመላው ኢትዮጵያዊያን አብን ብዙ ቁጥርና ጠንካራ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎችን ከመያዙም ባለፈ ከፍተኛ የሕይወት፣ የአካል፣ የኃብት መስዋዕትነት የተከፈለበት እና በሕዝብም ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ አገራችንና ሕዝባችን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለበት በዚህ ጊዜ በአብን የጉባዔ አባላት ውስጥ እየቀረበ ባለው የለውጥ (ሪፎርም) ጥያቄ ምክንያት በፓርቲው የተወሰኑ የበላይ አመራሮችና በጠቅላላ ጉባኤው አባላት መካከል የተፈጠረው ጊዜያዊ የኃሳብ አለመግባባት ለሕዝባችን ጥሩ ያልሆነ ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል እንረዳለን። ሆኖም ግን ፓርቲያችን አሁን ያለውን አቋምና የአደረጃጀት አቅም ይዞ የአማራን ሕዝብ የህልውና አደጋ ለመቀልበስና የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል የሚደረገውን ትግል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ወደፊት በማራመድ በኩል የሚቸገርበት ሁኔታ በመኖሩ ለውጥ (ሪፎርም) ማድረግና በመርህ የሚመራ ጠንካራ ተቋም የግድ እንደሆነ ጠቅላላ ጉባዔው ያምናል፡፡ በመሆኑም የአብን አባላትና ደጋፊዎች፣ በሀገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያላችሁ አማራዎችና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁኔታውን በመረዳት፣ የተሻለ ተቋማዊ ጥንካሬን እውን ለማድረግ ትግስታችሁና ድጋፋችሁ እጅግ በጣም እንደሚያስፈልገን በመግለፅ ለማንኛውም ተገቢ ትብብር ጥሪ እናቀርባለን፡፡ 5ኛ) ለመገናኛ ብዙኃን/ ሚዲያዎች እስካሁን በነበረው ሂደት ስለ ጠቅላላ ጉባዔው ድምፅ ለሆናችሁን ሁሉ ምስጋናችን እያቀረብን የተወሰኑ ከፍተኛ አመራሮችን አቅርባችሁ ቃለ ምልልስ የሰራችሁና ሌሎች ሚዲያዎችም ሕዝብ እውነቱን በግልፅ እንዲያውቀው በሚደረገው ሂደት ይሄንን ኮሚቴ በፕሮግራማችሁ በመጋበዝ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ስንል በአክብሮት እንገልፃለን፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ተወካይ ኮሚቴ!

Source: Link to the Post

Leave a Reply