ምስራቅ አማራ ዞኖች እየተስፋፋ የመጣው የአንበጣ መንጋን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እየሆነ እንደመጣ አርሶ አደሮችና የአካባቢው የመንግስት አመራሮች ገለጹ። የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ ለጉዳዩ ልዩ…

ምስራቅ አማራ ዞኖች እየተስፋፋ የመጣው የአንበጣ መንጋን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እየሆነ እንደመጣ አርሶ አደሮችና የአካባቢው የመንግስት አመራሮች ገለጹ። የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ አሻራ ሚዲያ መስከረም 25/2013 ዓ.ም ባህርዳር የአንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜዎች እየተከሰተ በሰብልና ግጦሽ መሬት ላይ ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዓመትም ከአዲሱ ዓመት መግቢያ ጀምሮ መንጋው በምስራቅ አማራ በሚገኙ ዞኖች ተከስቶ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ነው አርሶ አደሮች የሚናገሩት በአማራ ክልል የራያ ቆቦ ወረዳ አርሶ አደር አቶ ይማም መሀመድ ለዶይቼ ቬለ በስልክ እንደገለፁት የአንበጣ መንጋ በቦቆሎና በጤፍ ሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡የመከላከል ስራው በባህላዊና በኬሚካል እርጭት ጭምር ቢታገዝም የመንጋው ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል የአንበጣ መንጋው በዞኑ ራያና ሀብሩ ወረዳዎች በሚገኙ 19 ቀበሌዎች ተከስቷል ብለዋል፡፡ በ27 ሺህ ሄክታር ላይ መታየቱንና በ1 ሺህ 740 ሄክታር ማሽላና ጤፍ ሰብሎች ላይ ሙሉ በሙሉ ጉዳት ማድረሱንም ገልፀዋል፡፡ መንጋውን የመከላከል ስራ በአውሮፕላን በታገዘ የኬሚካል ርጭት ጭምር ቢሰራም አዳዲስ መንጋ በከፍተኛ መጠን በየቀኑ ይመጣል “ መጠኑ ከፍተኛ ነው፣ከቁጥጥርም ውጭ እየሆነ ነው” ሲሉም የችግሩን ክብደት አመልክተዋል፡፡ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊና የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ኢብሬ ከበደም አንበጣ በደዋ ሀረዋና በባቲ ወረዳዎች በሚገኙ ከ16 በላይ ቀበሌዎች በሚያስፈራ ሁኔታ ተከስቷል ብለዋል፡፡ በአውሮፕላንና በባህላዊ መንገድ የመከላከል ስራው እየተሰራ ቢሆንም በተለይ ባቲ ላይ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ አንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ በበኩላቸው አንበጣ በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ ዞኖችና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በከፍተኛ ሁኔታ መከፈቱን ጠቁመው ከፌደራል እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር የተጠናከረ የመከላከል ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይሁንእንጂ ከመንጋው ብዛት አኳያ ያሉት የመርጫ አውሮፕላኖች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንዳልተቻለ አብራርተዋል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስተር ዴኤታ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ በስልክ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ መንግስት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ 3ቱ የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴታዎች አንዱ ወደ ምስራቅ ሀረርጌና ሶማሌ ክልል፣ አንዱ ወደ አፋርና ሌለኛው በአማራ ክልል ተሰማርተው ሥራውን በቅርብ እየተከታተሉና እያስተባበሩ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ለስራው የሚያገለግሉ 3 አውሮፕላኖች መኪናዎች፣ ሞተር ብስክሌቶችና አስፈላጊው ኬሚካልም በበቂ ቀርቦ ስራው እተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የአንበጣ መንጋው መነሻ ከምዕራብ ህንድ፣ ከሰሜን ሶማሌ፣ ከየመንና ደቡብ ኤርትራ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መከላከል ከባድ እንዳደረገውም አቶ ወንዳለ ገልፀዋል፡፡ በቀጣይ ከተጠቀሱ አገሮች ጋር በመነጋገር በጋራ የሚሰራበት ሁኔታ እንደሚኖር ያመለከቱት አቶ ወንዳለ ተጨማሪ የእርጭት አውሮፕላን የሚገኝበት ሁኔታም እንደሚፈለግ አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ የግብርና ሚኒስቴር ከክልል መስተዳድሮች ጋር እየሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ግብርና ሚኒስቴርም ችግሩን ለመከላከል አስፈላጊውን ግብዓት ሁሉ እንደሚያቀርብ አረጋግጠዋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply