ምንም ዓይነት ግድያ ምሥጢርን አይደብቅም – ምሕረት ዘገዬ

በዚህች አጭር መጣጥፍ ውስጥ ደግሜ ላለመመላለስ ስል ሁለት ርዕሶችን በመጠኑ እዳስሳለሁ፡፡ የመጀመሪያው ከፍ ሲል ያስቀመጥኩት የዕለቱን ሁኔታ የሚገልጽ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ስለትምህርታችን የጥራት ደረጃ የታዘብኩትና ከሥር የቀረበው ነው፡፡

ኢንጂኔር ስመኘው በቀለ በመስቀል አደባባይ መኪናው ውስጥ ሞቶ መገኘቱን በአሁኑ ሰዓት በሰበር ዜናነት እየተነገረ ነው፡፡ ስለአሟሟቱ ሁኔታ ገና የተሰማ ነገር የለም፡፡ እርግጡ ሳይታወቅ ደግሞ እገሌ ገደለው ወይ አስገደለው ማለቱ በመሠረቱና እንደአካሄድ ህጋዊም ተገቢም ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እንደ አንድ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ተራ ዜጋ ግምቶችን ማስፈር ይቻላል፡፡

እናም በኔ ግምት ይህ ሰው ሊገደል የሚችለው በወያኔ መንደር ከሚሰነዘር የጥቃት ብትር እንጂ በሌላ ሊሆን እንደማይችል ከመቶ በመቶ በላይ እርግጠኛ መሆን እችላለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች አንዴ ቂም አይቋጥሩ እንጂ ከቋጠሩ እስከመቼውም ካለመርሳታቸውም በተጨማሪ አይገቡ ገብተው ያን ሰው ከመግደል አይመለሱም፡፡ ከመነሻቸው አካባቢ በሻለቃ ጃተኒ (መባፅየን) በኬንያ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የፈጸሙትን ግድያ ጨምሮ ከዚያም በፊትና ከዚያም በኋላ እስከዛሬይቷ ቀን ድረስ ወያኔዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሓን ዜጎችን ሕይወት ቀጥፈዋል፡፡ የመግደል ዕድሉን እስካገኙ ድረስ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብም ቢረፈርፉ የማይረኩ የሰው ደም ወልፍ የተጠናወታቸው የለዬላቸው ሰይጣኖች ናቸው፡፡ አሁን አሁን የሚገርመኝ ነገር ይልቁንስ እነዚህ አጋንንት እንደሰው ይሆናሉ ብለው በተስፋ የሚጠብቁ የለውጡ ጎራ ሰዎች ትግስት አይሉት ፍራቻ አለማለቁ ነው፡፡ ምን እስኪሆኑ ድረስ ይሆን የሚጠብቁት?

ኢንጂኔር ስመኝ ምናልባት ከግድቡ ጋር በተያያዘ ሊያወጣው ዳር ዳር የሚለው ምሥጢር ይኖርና በዚያ ምክንያት የገደሉት ይመስለኛል፡፡ ከጓደኞቼ እንደሰማሁት ለኢቲቪ ቃለ መጠይቅ ሊሰጥ በቀጠሮ ላይ ነበር አሉ፡፡ በዚያ ቃለ መጠይቅ ወቅት ምሥጢር ያወጣብናል ብለው ፈርተውም ሊሆን ይችላል በሳይቀድሙኝ ልቅደም ዛሬ ጧት ይህን አስከፊ እርምጃ የወሰዱበት –  ለወያኔዎች ለማንኛውም ችግር አቋራጭ የመፍትሔ ሥልታቸው ግድያ ነው – አነስ ካለም በህቡዕ ቦታ አሥሮ ዕድሜ ልክ እያሰቃዩ ማቆየት፡፡ ቀደም ሲልም ኢንጂኔር ስመኝን የቁም እሥረኛ አድርገውት እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች በግድቡ ምክንያት ብዙ የከበሩ ናቸው፡፡ የማይረባ ዕቃ እያቀረቡ ብዙ ቢሊዮን ብር አግበስብሰዋል፡፡ ማን ያውቃል ባልገባ ብረትና ስሚንቶም እንደገባ ተቆጥሮ ብዙ መዝብረው ይሆናል፡፡ ከጥራት አኳያም በርካታ ልፍስፍስና ዘመን ቀርቶ አንድ ክረምት የማይሻገሩ ውሽልሽል ሥራዎች በግድቡና በዙሪያው ተከናውኖ ይሆናል፡፡ የሆኖ ሀኖ ሰውዬው ሊያወጣው የተዘጋጀው ብዙ ምሥጢር እንዳለ መገመት ይቻላል፡፡ በመግደላቸው ግን ምሥጢሩን እስከወዲያኛው አፍነው ሊያቆዩት አይችሉም፡፡ ይዘገያል እንጂ ተደብቆ ዘላለሙን የሚቆይ ምሥጢር አይኖርም፡፡ ጊዜ ራሱም ያወጣዋል፡፡

በሌላም በኩል የዚህን ሰው ግድያ ስናይ ይህ የተሣካ የግድያ ሙከራ ብዙ አንድምታዎችን እደያዘ እንረዳለን፡፡ በመጀመሪያ የግድያው ቦታ መስቀል አደባባይ እንዲሆን መመረጡ “የቦምቡ ፍንዳታና የጠ/ሚኒስትሩ ግድያ ቢከሽፍም በምትኩና በቦታው ሌላ በግ አርደናል” ለማለት የፈለጉ ይመስላል፡፡ ሲቀጥልም “ኃይላችን ገና አልበረደም፡፡ ከኛ የግድያ ራዳር ውጪ የሚሆን የለምና ሁልሽም በዚህ ሰው መቀጣጫነት ተማሪ” ለማለት ፈልገውም ሊሆን ይችላል፡፡ ሲሰልስም “የፈለግነውን ብናደርግ ገልማጭ ቆንጣጭ የለንም፤ አሁንም ያሻንን ከማድረግ የሚያግደን አካል የለም” ማለታቸውም ነው፡፡ ይህ አዲሱ የለውጥ መንግሥት እነዚህ ባለጌዎች ምን እስኪሆኑ እየጠበቀ እንደሆነ በበኩሌ ማወቅ አልቻልኩም፡፡ “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም” ብለን አዲሱን መንግሥት በይፋ ከመተቸታችንና ተስፋ ከመቁረጣችን በፊት በጠራራ ፀሐይ በሀገራችን መዲና በአዲስ አበባ ይህን ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሰዎች በአስቸኳይ ወደ ፍርድ እንዲቀርቡ ቢደረግ ከተጨማሪ ጥፋትና ኪሣራ እንድናለን፡፡ ከሚገባው በላይ እሹሩሩ በመባላቸው ይሄውና ከመስከን ይልቅ የልብ ልብ እየተሰማቸው ድፍረታቸው ድንበር አጥቷል፡፡ “ጨው ለራስሽ ስትይ ጣፍጭ” እንዲሉ ነውና የነዶ/ር ዐቢይ ቡድን አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰደ ይህ ግድያ ነገ በማን እንደሚደመደም ግልጽ ነው፡፡ ለውጡ ከሸፈ ማለት ደግሞ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እንጂ ኢትዮጵያ ከሩዋንዳና ሦርያ በሚበልጥ የእሳት እቶን ላይ ትጣዳለች፡፡ ያኔ ከእሳት ለመትረፍ የሚኖረን ዕድል ከንፍሮ ወይም ከአሹቅ ጥሬ የመውጣት ያህል ነው፡፡ ለማንኛውም የስመኝን ነፍስ በገነት ያኑራት፡፡

እንደአጠቃላይ እውነት ግን እንዲህ እላለሁ፡፡ አንድ ድርጅትም ይሁን ግለሰብ ምሥጢር እንዳይወጣበት ብሎ ንጹሓን ዜጎችን ቢገድል ወይ ቢያስገድል ምሥጢሩን ይበለጥ ዘረገፈው እንጂ አልደበቀውም፡፡ ብዙ ምሣሌዎችን መጥቀስ ቢቻልም የሰማሁትን የበዓሉ ግርማን አገዳደል በመጠኑ ላስታውስ፡፡

እንደሰማሁት የተወሰኑ የደርግ ባለሥልጣናት – ከሊ/መንበር መንግሥቱ ዕውቅና ውጪ ነው አሉ – በዓሉን ለመግደል  ይወስናሉ፡፡ ሁለት ወታሮች እንዲገድሉ ግዳጁ ይሰጣቸዋል፡፡ እነሱ በሥውር ቦታ በዓሉን ገድለው በአገር አማን ወደመጡበት ሲመለሱ ሌሎች ሁለት ወታሮች እነዚህን ገዳይ ወታደሮች እንዲገድሉ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሀል የበዓሉ ገዳዮችና አስገዳዮች ማንነት የውኃ ሽታ ሆኖ ይቀራል፡፡ ሁሉም ነገር ተድበስብሶ ቀረ፡፡ ግን እስከ መቼ? ተደብቆ የቀረ ነገር የለም፡፡ በጊዜ ሂደት ሁሉም ታወቀ፡፡

መረዳት ያለብን አንድ እውነት አለ፡፡ በዓሉ ተገድሏል፡፡ ትልቁ እውነት እርሱ ነው፡፡ በዓሉን የገደለው ሰው/ቡድን ማንነት ሁለተኛ ጥያቄ ነው፡፡ ያንንም ማወቅ ብዙ ከባድ አይደለም፡፡ በጥርጣሬ የተጠርጣሪ ገዳዮችን ብዛት መጨመር ይቻል እንደሆነ እንጂ ዋናውን ተጠርጣሪ ገዳይ ማወቅ ብዙም ከባድ አይደለም፡፡ በመሆኑም በዓሉ መሞቱ እርግጥ ከሆነ ዘንድ የሚገድለው በጽሑፎቹ የተናደደ  የሥርዓቱ አንድ ወይም ጥቂት ባለሥልጣናት እንደሚሆኑ የማንም ግምት ነው፡፡ ስለዚህ የአራት ሰው ሕይወት የጠፋው በከንቱ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነት ማኪያቬሊያዊ የጭካኔ አካሄድ ከሀገራችን እንዲወገድ ሁላችንም ጥረት ማድረግ አለብን፡፡

በመሠረቱ በመገዳደል የትም መድረስ አይቻልም፡፡ በመገዳደልም ምሥጢርን ይበልጥ መዘክዘክ እንጂ መደበቅ የሚቻል አይደለም፡፡ የሚያዋጣን ብቸኛ መፍትሔ ችግሮችን በጤናማ የውይይትና ክርክር ሂደት ተደማምጦና ተግባብቶ በሰከነ ሁኔታ በሰላም መፍታት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው የእልህና የግድያ ጉዞ ዞሮ ዞሮ ሁሉንም አረንቋ ውስጥ የሚከት የጨለማ ጉዞ ነው፡፡

ወያኔ በአካል እስካሁኒቷ ቅጽበት እየገደለን ነው፡፡ አንድ ወንድማችንን ለአብነት ዛሬ አጣነው፡፡ ገና ይቀጥላል፡፡ ነገ ማንኛችንን እንደሚጥል አናውቅም፡፡ ከዚሁ ግድያ ጋር በተያያዘ ትልቁን ግድያ ደግሞ ቀጥዬ በምመለከተው ርዕስ አቀርባለሁ፡፡ ከግድያዎች ሁሉ ትልቁ ግድያ የምለው የአንድን ሀገር የትምህርት ሥርዓት እንክትክቱ እንዲወጣ ማድረግና በውጤቱም ደናቁርት ዜጎችን በብዛት ማምረት ነው፡፡ በዚህን ዓይነቱ ብልሹ የትምህርት ሥርዓት የሞራል ዕሤቶች አብረው ይሞታሉ፤ ሃይማኖታዊ ተቋማት፣ የጤና ተቋማት፣ ማኅበረሰብኣዊ የሞራልና የባህል ወጋግራዎች ተያይዘው ወደ ገደል ይገባሉ፡፡ የትምህርት ሥርዓት ተበላሽቶ በዚያ በተበላሸ የትምህርት ቧምቧ(አሸንዳ) የሚያልፉ ዳኞች፣ ጠበቆች፣ መምህራን፣ ኢንጂኔሮች፣ የማኅበራዊና የተፈጥሮ ሣይንስ ዶክተሮች፣ ዝቅተኛና ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎች፣ ሹፌሮች፣ ፓይለቶች፣ ወታደሮች፣ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ. ከሚጠበቅባቸው የአሠራር ብቃትና ሙያዊ ዲሲፕሊን ይወጡና ሀገር ጃርት እንደበላው ዱባ አካማሌ ትሆናለች – የደም ሥራቸው የሚሠራው በሙስናና በንቅዘት ከመሆኑም በተጨማሪ የሥራ ጥራት እንዘጭ ብሎ ሁሉ ነገር የብላኔ ይሆናል፡፡ ያኔ ሰዎች በቅርጽ እንጂ በይዘት ሰው መሆናቸው ያቆማል፡፡ ያኔ ሰዎች በሥነ ፍጥረት አቻዎቻቸው ከሆኑ ሌሎች እንስሳት እጅግ የሚያንሱ ወራዳ ፍጡራን ይሆናሉ፡፡ ሆዳሞች፣ ሰካራሞች፣ ሴሰኞች፣ ሌቦች፣ ቀማኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ወንጀለኞች፣ ከሃዲዎች፣ …. ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ዓይነቱ የአሥሽ ምቺው አባዜ ነፃ የሚሆኑ በጣም ጥቂት ናቸው – እነሱም መፈጣራቸውን እየተራገሙ በስቃይና በሰቀቀን የሚኖሩ ይሆናሉ፤ “ጌታየ ሆይ በዚህን ክፉ ዘመን ስለምን ፈጠርከኝ?” በሚል የዘወትር ምህላ ፈጣሪያቸውን የሚወቅሱ ይሆናሉ (አለደምቡና አለባህሉ የጀሶ እንጀራ፣ የሞራና የሙዝ ቅቤ፣ የሸክላ በርበሬ፣ የአህያና የበከተ እንስሳ ሥጋ እያበላ ለሞትና ለበሽታ የሚዳርግህን አጋሰስ ትውልድ ከመረቅህ በርግጥም አንተ ብፁዕ ነህ)፡፡ በሀገራችን እያየን ያለነው አሳዛኝ ትርዒት እንግዲህ ይህንን ነው፡፡

 

ሁለተኛው ርዕሴ – Nature Gaves for Ethiopia you!

 

በክፍል ውስጥ የማስተምራቸውን ተማሪዎቼን አነጋገር የኮረጀ አንድ ምሁር በመምህራንና በጠ/ሚኒስትሩ የሰሞኑ ስብሰባ ላይ ተመለከትኩና ትንሽ ፈገግ ስላደረገኝ ይህችን ማስታወሻ ልጽፍ ተነሳሁ፤ አነሳሴ የደረስንበትን የማነስ ደረጃ ለመጠቆም እንጂ በሰው ስህተት ለመዝናናት እንዳልሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ የማይሳሳት ደግሞ የለም፡፡ ሁላችንም በአንድ ወይ በሌላ አጋጣሚ እንሳሳታለን፡፡ ስህተታችንን ስናውቅ ወይም ሲነገረኝ ግን ለመታረም ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ መወገድ ያለበት ነገር ስህተት መሥራትን እንደባህል ቆጥረን በስህተት መንገድ ሆነ ብለን መንጎድን ነው፡፡ እንጂ ከ”ሰው ስህተት ከብረት ዝገት” አይጠፋም፡፡

በነገራችን ላይ በዚህ ዘመን የምንጽፍበት ነገር በዛና ተቸገርን፡፡ ግዴላችሁም እነዚህ ሰዎች የርገረም አድርገውናል፡፡ “የርገረም” ማለት በተወለድኩበት አካባቢ ዘዬኣዊ አገላለጽ “ብልሽትሽቱ የወጣ” ማለት ነው፡፡ ከኔ ሠፈር ራቅ ባሉ ሌሎች የማውቃቸው አካባቢዎች ደግሞ “አካማሌ” ይላሉ፡፡ ያው ነው ትርጉሙ፡፡ አንድ ሰው ወይም አንድ ሁኔታ ሲግማማና ውጥንቅጡ ሲወጣ እነዚህን መሰል ቃላት በመግለጫነት ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ለማንኛውም ወያኔዎች አካማሌ አድርገውን ሊጠፉ የተዘጋጁ ይመስላሉ – የርገረም አድርገውን፡፡ አሁን ከመሸም ቢሆን ተባብረን ይህን የጥፋት ዕቅዳቸውን በጋራ ካላመከንነው ታያላችሁ ማንኛችንም አንተርፍም፡፡ መድኃኒታችን የኛው ትብብርና ፍቅር ነው፡፡ ምርጫችን በየተራ ማለቅ ወይም ተባብሮ ጠላት ወለድ ችግሮችን በመታገል ሁላችንም ነፃ የምንሆንበትን ነፋሻ አየር መፍጠር ነው፡፡ በብዙ ሺዎች የሚገመቱ ጠላት ያሰለጠናቸው ነፍሰ ገዳዮችና ቤትና አካባቢን በእሳት እያጋዩ የሚሰወሩ ወምበዴዎች ሀገር ምድሩን እያጥለቀለቁ መሆናቸውን መንግሥት እያወቀ መቶ የማይሞሉ ጥቂት ሽፍቶችን እንክ እንክ እያለ ማባበሉ ለለውጡ እርምጃ ውጤታማነት ደግ አይደለምና ይታሰብበት፡፡ በአካልም በመንፈስም እየገደሉን እንዲቀጥሉ አንፍቀድላቸው፡፡

የምሁራንን ስብሰባ በኢቲቪ እያየሁ ሳለ አንዱ ቆፍጣና ጎፈሬ መምህር – መምህር ይሆን ይሆናል መቼም –  መነጋገሪያውን ተቀበለ፡፡ ሳይቸግር ጤፍ ብድ እንዲሉ ላያዛልቀው ንግግሩን በእንግሊዝኛ ጀመረ፡፡ “አሃ! ይቺ ሰው አማርኛ የምትጠላ ወይ ደሞ ባማርኛ ከምትናገር በእንግሊዝኛ ብትናገር እንደሚቀላት የተረዳች ኃይለኛ ምሁር ናት!” አልኩና በጉጉት መከታተሌን ያዝኩ፡፡ ውሸት መናገር ምን ይሠራል? መደባበቅስ ምን ይፈይዳል? አፈርኩ፡፡ ምሁሪት እንዲህ እያለች ቀጠለች፡፡ (የተነገረውን እንደወረደ ስለጻፍኩት ‹ኤዲት› አይደረግ(ብኝ)፡፡)

… for giving me the chance, I would like to say this:- you know, nature gaves Arab countries oil, nature gaves Uganda Victoria Lake; nature gaves Eritrea Dahlak Massawa; nature gaves Kenya Mombasa; nature gaves for Ethiopia you.(የቀለጠ ጭብጨባ) …. ቀጠለች ምሁሯ… one of my friend….

ታዲያ ምን ይጠበስልህ? የሚለኝ ካለ ለጊዜው ምንም ነገር እንዲጠበስልኝ አልፈልግም – በቅርቡ ነው ምሣየንም የበላሁት፡፡ ግን ግን የደረስንበትን ደረጃ ታዘቡ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ብዙ ቦታ እንደታዘብኩት በስህተቱ የማይቆጭ፣ መሳሳቱን ስትነግሩት ደግሞ “ዋናው መግባባቱ እንጂ ምን ጣጣ አለው? ምን ችግር አለው? አቦ አታካብዳ!” የሚለው መብዛቱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እንግሊዝኛ ሞታ የቀብር ሥነ ሥርዓቷም ሊፈጸም ጸሎተ ፍትሓቱን የሚመሩት አቡን ከታላቋ ብሪጣንያ እስኪመጡ  እየተጠበቀ ነው፡፡ ከምንም ያልሆነ ትውልድ እያፈራን የርገረም ሆነን መቅረታችነ ያሳዝናልኝ – በጎንደር አማርኛ፡፡ ኤዲያ ለምን ዓይነት ሀገር ውሽጥስ ተፈጠርኩ እንዴ? – የትግርኛችን ተፅዕኖስ ለምን ይቅርብኝ…!

Leave a Reply