“ምን ዓይነቱ ጀዝባ ነው…”… “ቁረጠው …” ይነጋል በላቸው

“ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት” የሚለው ግሩም ብሂል ዱሮ ቀረ፡፡ ዛሬ ዛሬ እምባጮም ደደሆም ብሣናም ለታቦትነት ሳይመረጡ አይቀሩም፡፡ እንደአቢይ አህመድ ያለ ሀሰተኛና አስመሳይ ጠ/ሚኒስትር ባለባት ሀገራችን ውስጥ ብዙ ነገሮች ተዘበራርቀው በጭንቀት ምክንያት ደህና እንቅልፍ መተኛትም ለአንዳንዶቻችን ብርቅ ሆኗል፡፡ የደላቸው ደግሞ ዛሬን ማደራቸውን ሳያውቁ ስለነገ ብዙ ይጨነቃሉ፤ ያቅዳሉ፡፡ እየተሳለልን የሚገኘው ሠይፍና ጎራዴ ግን ልዩና ምሕረት-የለሽ ነው፡፡ ወዮ! እንበል፡፡ ወዮ! ለሀገራችን!

አቢይ አህመድ የሚፈነጭባት ኢትዮጵያ ሰው የሌላት ይመስል የቅቤ ገበያ ሆናለች፡፡ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይል በትረ ሥልጣኑን ተቆጣጥሮት የሚታዬው ጉድ ሁሉ ያስደነግጣል – አንዳንዴ እንደ አንዳንድ የቅርብም የሩቅም ሰዎች “ምነው ግዴለሽ በሆንኩ” እላለሁ – አንዳንዴም “ምነው ቀደም ሲል ተወልጄ ዕድሜየ ዛሬ ላይ ባልደረሰ” እላለሁ፡፡ ቀኑ መሽቶ የሚነጋው በተዓምር ነው፡፡ በብሔራዊ ሚዲያዎች ሳይቀር አንዱን የብሔር ስም በቀጥታም ባይሆን በተዛዋሪ እያነሱ “በለው፤ እረደው፤ ከክልልህ አስወጣው…” ብሎ መፎከርና ማስፎከር የየዕለት ገጠመኛችን ከሆነ ውሎ አደረ፡፡ በትዕዛዝና በመንግሥት በጀት በሚደገፍ የውሎ አበል በሚጠሯቸው ሰልፎች በጠብ ያለሽ በዳቦ ንጹሓን የሕዝብ ልጆችን ያስፈራራሉ፤ ያስራሉ፤ ያሰቃያሉ፤ ይገድላሉ፡፡ ሀፍረትና ምን ይሉኝ የሉም፡፡ ካለፈ መማርም እንዲሁ ዕርም ሆኗል፡፡ ጥጋብ ዕብሪትን፣ ዕብሪትም ዐመፃን እየወለዱ ሕዝብን ከሕዝብ ለማፋጀት የተያዘው አጀንዳ በስፋት እየተሄደበት ነው፡፡ አጠቃላይ ዕልቂት ቢነሳ ወይም ሲነሳ አንድን ወገን ብቻ ለይቶ የሚያጠቃ ይመስል የዕልቂቱ መጀመር ለወር-ተረኞቹ የሠርግ ድግስ ያህል በጉጉት የሚጠበቅ ሆኗል፡፡ ያሳዝናል፡፡ የምናየውና የምንሰማው ሁሉ ተረት ተረት እንጂ የእውን አይመስልም፡፡ የዚህ ሁሉ ድራማ ዋና አጋፋሪ ደግሞ የአክራሪ ኦሮሞዎች ቁንጮ የሆነው፣ ከሥልጣኑ በላይ የማይሞቀውና የማይበርደው  አቢይ የሚባለው ጉደኛ ፍጡር ነው፡፡ ይህ ሰው የተምታቱ ስብዕናዎች ዋሻ ሆኖ አንድ አባውራ “ዕብድ እህል ገዝቼ ሚስቴን አሳበድኳት” እንዳለው ሁላችንንም እያሳበደን ነው፡፡

ስለዚህ ጠ/ሚኒስትር ተብዬ ከመነሻው ጀምሮ ብዙዎች ብዙ ብለዋል፡፡ በመልከ መልካምነቱም፣ በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀቱም፣ አብዛኛው ቆርጦ ቀጥል መሆኑ እየታወቀም ቢሆን በአነጋገር ለዛውም የሚማረከው ወገን ደግሞ ከእንቅልፉ ባለመንቃት በዚህ ሰውዬ ላይ ተስፋውን ጥሎ አሁንም ድረስ ይጃጃላል – አለመታደል ነው፡፡ እኛ ሰው ባይሰማን እግዚአብሔር ይሰማናል፤ ሰምቶም ዝም አይልም፡፡ ቋቱ ሲሞላ ፍርዱን መስጠቱ ሃቅ ነው፡፡ አንድ ነገር ሲዘገይ የቀረ መምሰሉ ግን ብዙዎችን እያነሆለለ ላልጠበቁት ጉዳት ይዳርጋቸዋል፡፡

ልጅ ይውጣለትና ዘማሪ ዶክተር ደረጀ ከበደ ሰሞኑን የጻፈው ጽሑፍ እጅግ ስሜት ኮርኳሪ ነው፡፡ የአቢይን የመሰለ ብልሹ ተፈጥሮ በሚመለከት በግሩም አቀራረብ የጻፈውን ይህን መጣጥፍ በዚህ የዩቲብ አድራሻ ገብታችሁ ብታደምጡት ታተርፉበታላችሁ፡- “የጨለማው ሶስትዮሽ ቀውስ (The Dark Triads) Narcissism, Machiavellianism & Psychopathyየጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ ማንነት”፤  http://www.youtube.com/shorts/tw0sgM3gZbc

አልባሌ ሰዎች ወደላይ ሲወጡ ሁነኛ ሰዎች ወደታች ይወርዳሉ፡፡ ያኔ ሀገርም ሕዝብም ውድቀታቸው ይፋጠናል፡፡ በሀገራችን እየሆነ ያለው ደረቅ እውነት ይሄው ነው፡፡ ጥበብና ዕውቀት ወደጓዳ ገብተው ተከተቱ፡፡ ዱላና ጠበንጃ ቤተ መንግሥት ገብተው መላ ሀገሪቷ ላይ ወጧ እንዳማረላት ሴት ተውረገረጉ፡፡ በጠበንጃ ብቻ የልብ መሻታቸው የሚገኝ መስሏቸው ለ24 ሰዓት ዱላቸው የማይለያቸው የጨለማው መንግሥት ታዛዥ ደናቁርት ወታደሮች ሕዝብን ማንገላታትና መረሸን ሥራየ ብለው ተያያዙት – ልክ እንደወያኔው፡፡ ዘረኝነትን ጨምሮ በሥነ ልቦናና በአእምሮ ደዌያት የተመቱት የበላይ አመራሮች ደግሞ የብልጭልጩ ዓለም ቁሣዊ ሀብት ንብረትና የሆዳም ማይማን አጀብ ኅሊናቸውን አሳውረዋቸው ወያኔ በተከለው ድንኳንና በጣለው ዳስ ይሞላፈጡ ገቡ፡፡ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ያን ሁሉ የሕይወት መስዋዕትነት የከፈለው የወያኔን ሥርዓት በአዲስ ዘር-ተረኝነት ለማስቀጠል ይመስል “በህገ መንግሥታችን የመጣ ባይናችን መጣ” የሚሉን እነዚህ ጉዶች ሀገራችንን የገደል አፋፍ ላይ አስቀምጠው የፈንጁን ካምሱር ይስቡት ያዙ፡፡ መጨረሻቸውን የሚያይ የታደለ ነው፤ ከፈጣሪዎቻቸውና ከአሳዳጊዎቻቸው ወያኔዎች የነሱ የከፋ መሆኑ በጣም ግልጽ ነውና፡፡…

አቢይ አህመድ ሊታዘንለትና ህክምናም ማግኘት የሚገባው የአእምሮ በሽተኛ ስለመሆኑ ዶክተር ደረጀ በግሩም ሁኔታ ገልጾታል – “ሊታዘንለት” የምትለዋን እኔ የጨመርኳት መሰለኝ፡፡ አዎ፣ እሱም ያሳዝናል፤ ወዶ እንዲህ አይሆንምና፡፡ ቀደም ሲል ይሄው በሽተኛ ጠ/ሚንስትር በአንድ መድረክ ላይ አንድን ምሥኪን ዜጋ በአደባባይ ሲሳደብ የተቀረጸውን የምስልና የድምጽ ማስረጃ አንድ ወዳጄ በኢሜል ልኮልኝ ሳየው በሀገራችን ዕድል ክፉኛ አዘንኩ፡፡ እርግጥ ነው ሰው እንደየሁኔታዎች ተለዋዋጭ ባሕርይ እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ በቤታችን፣ በመሥሪያ ቤታችን፣ በመዝናኛ ቦታዎች፣ በሞቅታ፣ በለብታ … በሀዘንና በደስታ ወዘተ. ሰው ነንና የተለያዩ ስሜቶችና የስሜት መገለጫዎች አሉን፤ እነዚህ ጠባዮች በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታ የሚገዙ መሆናቸውን ደግሞ አንዘነጋም፡፡ ሆኖም የፈለገውን ያህል የሰዎች ጠባይ ቢለዋወጥ ፕሮቶኮሉን ጠብቆ ለሕዝብ ቃለ መጠይቅ እያደረገ ያለ አንድ የሀገር መሪ ጫት ቤት የተቀመጠ ይመስል በዚያ መልክ “ምን ዓይነቱ ጀዝባ ነው … ‹ቁረጠው›“ ብሎ እንደተራ የቡና ቤት ሴት ሲሳደብ መስማት ያስደነግጣል፤ ያሣፍራልም፡፡ እመራዋለሁ የሚለውን ሕዝብም መናቅ ነው (‹ቁረጠው› ማለቱ ስድቡ “ለሕዝብ አይተላለፍ” ለማለት ነበር፤ ሆኖም “ከአፍ ከወጣ አፋፍ” ነውና ሰማነው፤ አየነውም)፡፡ ለነገሩ አምባገነኖች ለይምሰል ካልሆነ በስተቀር ከሥልጣናቸው ውጪ የሚያከብሩትና የሚያፈቅሩት አንዳችም ነገር የላቸውም፡፡ እምብዝም ላልተለመደ ግልጽነቴ ይቅርታ ይደረግልኝና በዚህ ዓይነት እንደሐረር ወጣቶችና ጎልማሦች ልማዳዊ አነጋገር ሁላችንንም “እናታችሁን ‹ልቀፍላችሁ›…” እንደማይለን ምንም ዋስትና የለንም፡፡ ባለጌን በተለያዩ አጋጣሚዎች እንለየዋለን፡፡ ይህ አስመሳይ ሰው በዚያች አጋጣሚ ብቻ እንዴት ያለ የተዛነፈና የበሸቀጠ ጠባይ እንዳለው መረዳት አይከብድም፡፡ መጥኔ ለቤተሰቡ፤ እንደእግዚአብሔር ፈቃድ እኛስ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሳንገላገለው የምንቀር አይመስለኝም – የነገሮች ፍጥነት ለዚህ ግምቴ ዋቢ ናቸው – ዙሩን እጅግ አክርረውታል፡፡ በመተከልና በብዙ የኦሮሞ አካባቢዎች ብዙ ደም እየጮኸ ነው፤ ብዙ ግፍና በደል እየተፈጸመ ነው፡፡ እንደሰው አይቸኩልም እንጂ ይህን የሚያይ ፈጣሪ ደግሞ አለ፡፡የፈጣሪን ፍትኅ ያለማስተዋል በሽታ አዙሪት ውስጥ እየከተተ በተደጋጋሚ ያንደባልለን ያዘ እንጂ የሱ ፍርድማ አትቀርም፡፡…

በዚህ አድራሻ ግቡና እስኪ እናንተም ትንሽ ተናደዱ፡ https://www.youtube.com/watch?v=gbS36fURm2E

“ምን ዓይነቱ ጀዝባ ነው…”… “ቁረጠው …”

 ይነጋል በላቸው ([email protected])

Leave a Reply