ምክር ቤቱ በአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ውይይት አካሄደ

ምክር ቤቱ በአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ውይይት አካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተካሄደበት፡፡

ውይይቱ የተካሄደው በጅግጅጋ የፌደራል የዲሞክራሲ ተቋማት የጋራ ምክክር መድረክ ላይ ነው ተብሏል፡፡

በቀጣዮቹ 5 ዓመታትም ለማከናወን ያቀዳቸውን ተግባራት የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ፀሀፊ ዶክተር ሄኖክ ስዩም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በዕቅዱ ውስጥ ጥራትና አግባብነት ያላቸውን ህጎችን የማውጣት፣ ዕወቀትንና መረጃን መሰረት ያደረገ የክትትልና ቁጥጥር፣ ምክር ቤቱን ተደራሽ የማድረግ፣ የህዝብ ውክልና፣ የምክር ቤቱን አቅም የመገንባት፣ የፓርላማን ዲፕሎማሲን የማጠናከር፣ ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂንና የመረጃ አያያዝ ስርዓት የማዘመን እና የዘርፈ ብዙ ስራዎች መካተታቸውን አብራርተዋል፡፡

በቀረበው የምክር ቤቱ የ5 ዓመት መሪ ዕቅድ ላይም ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የቀረበው ዕቅድ ጥሩ መነሻ እና ሊሰራ የሚችል መሆኑም በተሳታፊዎች ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በዕቅዱ ውስጥ በሚገባ ሊታዩ ይገባል የተባሉ አስተያየቶችም ተሰንዝረዋል፡፡

ከእነዚህ መካከልም በምክር ቤቱ የሚወጡ ህጎች የጥራት መጓደል፣ የምክር ቤቱን ስራዎች ታች ድረስ ላለው የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ያለማድረግ፣ ለፓርላማ ዲፕሎማሲ ስራዎች ትኩረት አለመስጠት፣ የምክር ቤት አባላትን አቅም በተፈለገው ደረጃ አለመገንባት፣ የዲሞክራሲ ተቋማትን ያለማጠናከር እና በክትትልና ቁጥጥር ላይ ተጠያቂነትን ያለማስፈን ችግሮች በዋናነት ይገኙበታል፡፡

ለቀረቡት ጥያቄዎች የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በምክር ቤቱ በሚወጡ ህጎች ላይ የጥራት መጓደል በመኖሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በርካታ ውይይቶች መደረጋቸው ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥራት ያላቸውን ህጎች ለማውጣት የሚያግዝ የህግ ማርቀቅ ማንዋል የተጠናቀቀና በቅርቡም ስራ ላይ የሚውል መሆኑን ምለሽ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሚወጡ ህጎች ዙሪያ የሚያማክር የህግ ኮሚሽን ወይም የህግ ማዕከል አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ሚዲያዎችን ጨምሮ የምክር ቤቱን ስራዎች በምክር ቤቱ ዌብ ሳይት ተደራሽ የማድረግ፣ በሀገሪቱ ነጻ ሆነው የሚሰሩ የዴሞክራሲ ተቋማት መኖራቸው ወሳኝ በመሆኑ ነጻ ሆነው የሚሰሩ ፍርድ ቤቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ የተጠናከሩ ሚዲያዎች እንዲኖሩም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም የውጭ ዲፕሎማሲን የማጠናከር፣ የአባላትን አቅም የሚገነባና የሚያማክር ቢያንስ አንድ ማዕከል እንዲኖር ጥረት እንደሚደረግም አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱም የተሰጠውን ተግባራት ያልተወጣውን አካል በሚገባ ገምግሞ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታልም ነው ያሉት፡፡

ዕቅዱ ከተሳታፊዎች የተነሱ አስተያየቶችን በግብዓትነት በመውሰድ ዳብሮ ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚላክ መግለጻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

The post ምክር ቤቱ በአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ውይይት አካሄደ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply