በዛሬው እለት 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን በ22ኛ መደበኛ ስብሰባው የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
የራስገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በሚሰጣቸው ተቋማዊና አስተዳደራዊ ነጻነት በመጠቀም በመማር ማስተማር እንዲሁም በጥናትና ምርምር ስራዎች ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት የሚያከናውኑ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያላቸው እንዲሆኑ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እንደሆነ የተከበሩ ነገሪ (ዶ/ር) ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ ላይ አንስተዋል፡፡
ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በስፋት የቀረቡ ሲሆን፤ ረቂቅ አዋጁ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች አነስተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ከፍለው መማር ስለማይችሉ ከሌሎች እኩል የትምህርት እድል እንዳያገኙ ሊያደርግ ስለሚችል አዋጁ ጊዜውን የጠበቀ አይደለም የሚሉት አስተያየቶች በስፋት ተነስተዋል፡፡
በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ አዋጁ በሀገሪቱ የተጀመረውን የትምህርት ጥራት ሪፎርም የሚያጠናክር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ከተለመደው የቢሮክራሲ አሰራር በመውጣት ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንዲሰሩ የሚያስችላቸው አዋጅ እንደሆነም ነው የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ያስረዱት፡፡
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ አዋጁ ዩኒቨርሲቲዎች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲሰጡና የሚጠኑት ጥናቶችም ችግር ፈቺ እንዲሆኑ የሚያግዝ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
አነስተኛ ገቢ ያላቸው ተማሪዎች ጫና እንዳይኖርባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉን የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ጠቁመው፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ወደ ራስ ገዝነት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑንና በሂደት ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችላቸውን መስፈርት እንዲያሟሉና እንዲወዳደሩ ያስችላል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ ዩኒቨርሲቲዎች የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዲያጎለብቱ የሚያስችል መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ገልጸው፤ ነገር ግን የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የፕሬዚዳንቶች ሹመት፣ የኦዲት ስርዓት እንዲሁም ሁሉንም ማህበረሰብ አካታች እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስችሉ ደንብና መመሪያዎች ሊዘጋጁ እንደሚገባቸው አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በአራት ተቃውሞ እና በ13 ድምጸ ተአቅቦ አዋጅ ቁጥር 1294/2015 ሆኖ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም
Source: Link to the Post