ምክር ቤቱ ጥቃቅን ልዩነቶችን በመተው ግድቡን በፍጥነት ለመጨረስ ሁሉም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቀረበ

ምክር ቤቱ ጥቃቅን ልዩነቶችን በመተው ግድቡን በፍጥነት ለመጨረስ ሁሉም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሚያለያዩ ጉዳዮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉ ስለሚበዙ ጥቃቅን የውስጥ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በፍጥነት ለመጨረሽ ሁሉም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቀረበ፡፡

የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸው ጥረት ሥር ከሰደደው ድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ በአንድነት ቆርጠው መነሳታቸውን የሚያረጋግጥ የኢትዮጵያዊ ማንነት መገለጫ መሆኑን ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡

ግድቡ በሕዝቦች እውቀት፣ ጉልበትና ሃብት በሉዓላዊ ምድር የሚገነባ አንጡራ ሃብት ነው ያለው ምክር ቤቱ፤ የሌሎች የታችኛው የተፋሰስ ሃገራትን ፍትሐዊ አጠቃቀም መርህን በማክበር እየተገነባ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

ይህንን እውነታ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለግብፅ በመወገን ኃላፊነት በጎደለው አኳኋን ያስተላለፉት መልዕክት ከአንድ “ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህና ለእኩልነት ጥብቅና እቆማለሁ” ከሚል ከትልቅ ሃገርና ሕዝብ መሪ የማይጠበቅና የማይመጥን ነውም ብሏል ምክር ቤቱ፡፡

እንዲሁም የፕሬዚዳንቱ ንግግር ከግል ስሜትና አቋም አልፎ የአሜሪካ ሕዝብን አቋም ይወክላል ብለን አናምንምም ነው ያለው፡፡

የፕሬዚዳንቱ ንግግር የኢትዮጵያውያንን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የበለጠ የሚያጠናክር፣ ግድቡን በላቀ ሕዝባዊ ተሳትፎ በፍጥነት በመጨረሰ ለማስመረቅና ለበለጠ አንጸባራቂ ድል ለመብቃት የሚያበረታታ መሆኑንም አንስቷል፡፡

በፍትሓዊ ተጠቃሚነት መርህ በሕዝቡ የላቀ ተሳትፎ እንደ ሀገር የሚሰሩ ሥራዎችን ለመስራት አሁንም ሆነ ወደ ፊት ማንም ሊያቆመው እንደማይችል ሊታወቅ ይገባልም ብሏል ባወጣው መግለጫ፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ከሚያለያዩ ጉዳዮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉ ስለሚበዙ ጥቃቅን የውስጥ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው እና ወንድማማችነትንና አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባቸውም አውስቷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ለሃገር ግንባታ ለሚጠቅሙና ከህልውና ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ህዝቡ የሚፈለግበትን መስዋዕትነት በመክፈል ግድቡን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በሚችለው አቅም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪውን አቅርቧል፡፡

The post ምክር ቤቱ ጥቃቅን ልዩነቶችን በመተው ግድቡን በፍጥነት ለመጨረስ ሁሉም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቀረበ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

This Post Has One Comment

Leave a Reply