ምድራዊው ገሃነም | ጌታቸው ሽፈራው

በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ “ገሃነም እሳት” የሚባለው፣ የሰው ልጅ በምድር ላይ የፈጸማቸውን የኀጢያት ሥራዎች በንሰኀ ሳያሽር ህይወቱ ካለፈ፣ ነፍሱ ቅጣት የምትቀበልበት የስቅየት ቦታ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህም ሆኖ ግን፣ በነቢብ ከሚታወቀው ከዚህ የክፉ ሰዎች እስራት ቦታ፣ ብዙ እጥፍ የበረቱ ማሰቀያዎች በምድራዊ አምባገነን መንግሥታት ተዘጋጅተው፡- ተቃዋሚዎቻቸውን፣ ለሃቅ የሚቆሙ ጋዜጠኞችን፣ በሃሳብ የተለዩአቸውን…

በአጠቃላይ የዓይናቸው ቀለም ያላማራቸውን ዜጎች የምድር ፍዳ ሲያስቆጥሩ እንደነበረ ከተረጋገጡ የታሪክ ገጾች አንበበናል። በእኛዋ ኢትዮጵያችንም ቢሆን፣ ከተፈራረቁ አምባገነን ሥርዐታት በበቂ የሰማናቸውና የታዘብናቸው የስቃይ ጠባሳዎች መኖራቸው ርግጥ ነው። በተለይ፣ በደርግ ዘመነ መንግሥት የተፈጸሙት በስፋት የሚዲያ ሽፋን እንዲያኙ ከመደረጉ በዘለለ፤ አጥፊዎቹ በሕግ ተጠይቀው እንደየ ድርሻቸው እስከ እድሜ

ልክ የሚደርስ ፍርድ ተላልፎባቸውና ቅጣታቸውን ጨርሰው መውጣታቸው የቅርብ ታሪካችን ነው።

ከዚህ በተቃራኒው፣ የደርግ ዘመንን የቀበሌ ሊቀ-መንበር እና አብዮት ጠበቂ ሳይቀር፣ ለፍርድ ያቀረበው ሕወሓት-መራሹ ኢሕአዴግ፣ ከደርግ እጅግ የከፋ ሰቆቃና በደል ከመፈጸም አልተገታም። ከዚህ አኳያም ቅስምን የሚሰብረው እና ግፉአንን ለሁለት ሞት የሚዳረገው፣ ያንን ሁሉ ስቀየት የፈጸመው ፓርቲም ሆነ ሹማምንቱ በሕግ ሊጠየቁ ቀርቶ፣ ስለ ጉዳዩ በይፋ የሚናገር እንኳ አለመኖሩ ነው። ይህንን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ የቆጠረው የሰቆቃው መሃንዲስ ትሕነግም፣ ወንጀሉን ገልብጦ ራሱን በተጎጂነት ለማቅረብ በመሞከር፣ በሰለባዎቹ ቁስል ላይ እንጨት እስከ መስደድ ደፍሯል።

ኢሕአዴግን የተካው ብልፅግናም ቢሆን፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ‹ይጠቅሙኛል› ያላቸውን በማዕከላዊ እና አዲስ አበባ በሚገኙ የተወሰኑ ማሰቃያ ጉሮኖዎች ከተፈጸሙት ውስጥ፣ ጥቂቱን ብቻ ጨልፎ በሚዲያ አጯጩኾ ሲያበቃ፤ በመላ አገሪቱ የተፈጸሙ የከፋ ሰቆቃዎችን እንዳላየ አልፎ ፋይሉን ዘግቶታል።

የሆነው ሆኖ፣ በዚህ ዐውድ በዋንኛነት የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመውን ሰቆቃን እና ከሞት በኋላ ይገጥማል ተብሎ ከሚወራለትም ገሃነብ የከፉ የነበሩትን ማጎሪያዎች ጨርፈን እንመለከታለን።

ሰቆቃ በተራራማዎች ሥፍራ

 በ2013 ዓ.ም አንድ ታዋቂ ሰው፣ በወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች ላይ ከአርባ ዐመት በላይ የተፈጸመው በደል ይፋ እንዲወጣ የተለያዩ የአካባቢው ነዋሪዎችን ቃለ መጠይቅ የሚያርጉ ባለሙያዎች አፈላልጎ ይልካል። እነዚህ ባለሙያዎችም እየተዘዋወሩ ቃለ መጠይቅ ማድረግ ሲጀምሩ፣ በሰው ልጅ ላይ ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ስቅየት ስለመፈጸሙ የሚያመላክቱ መረጃዎችን እያለቀሱ ከሚናገሩ ከራሳቸው ከሰለባዎቹ እና ከቤተሰቦቻቸው ያደምጣሉ። በሰሙት ነገር እጅግ በማዘናቸውም፣ የእምባ ጎርፍ ሳያስቡት ያጥለቀልቃቸዋል። ምክንያቱም፣ በወቅቱ አንዳቸውም፣ እዚህ ኢትዮጵያ ወልቃይት ጠገዴ ውስጥ እንዲህ ያለ ገሀነም ይኖራል ብለው ፈጽሞ አልገመቱም። ሁሉም ቃለ መጠይቅ ያደረጉላቸው ሰዎች ያወሩት ስለ ዝነኛውና

በተለምዶ “ገሃነም” ተብሎ ስለሚጠራው የትሕነግ እስር ቤት ነበር።

ትሕነግ፣ በርካታ ንፁሃንን ያጉረባቸው እነዚህ አሰቃቂ እስር ቤቶች፣ የጅምላ መቃብሮችንም እንዲይዙ አድርጎ መሥራት የጀመረው ገና ወልቃይት ጠገዴን ከረገጠበት ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ፣ ከአራት ኪሎ ከተባረረ በኋላ የወጡ መረጃዎች አስረግጠዋል። እስር ቤቶቹ እንዲሠሩ ያደረገው ደግሞ፣ የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው በጅምላ ባፈሳቸው በራሳቸው በታሳሪዎቹ ነው። እነዚህ ግፉአን አማራጭ ስላልነበራቸው ፍፃሜውን ለማያውቁት ዐመታት በቁማቸው የሚቀበሩበትን ጠባብ የምድር ውስጥ የእስር ክፍሎች ወደታች ቆፍረው እና ድንጋይ ፈልጠው ከሠሩ በኋላ፣ ለተራዘመ ጊዜ ማቅቀውባቸዋል።

Continue reading

 

The post ምድራዊው ገሃነም | ጌታቸው ሽፈራው appeared first on ፍትሕ መፅሔት.

Source: Link to the Post

Leave a Reply