ምግባረ ሰናይ ድርጅቱ በ95 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጪ የሚተገበርና ከአማራጭ እንክብካቤ በሚወጡ ወጣቶች ላይ የሚያተኩር ፕሮጀክት አስጀመረ

ማክሰኞ መስከረም 10 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ኤስ.ኦ.ኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ በ95 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጪ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 11ዱ ክፍለ ከተሞች ላይ የሚተገበርና ከአማራጭ እንክብካቤ በሚወጡ ወጣቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት በስካይ ላይት ሆቴል በይፋ አስጀምሯል።

“Leave no youth behind” የተሰኘው ይህ ፕሮጀክት በክፍለ ከተሞቹ በሚገኙ 1 ሺሕ 400 ወጣቶች ላይ የሚተገበር ሲሆን፤ የፕሮጀክቱ ዋንኛ አላማም ከተለያዩ አማራጭ እንክብካቤ የሚወጡ ወጣቶች ራሳቸውን የሚችሉ እና ምርታማ የማህበረሰብ ክፍል እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑን የኤስ.ኦ.ኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ሳህለማርያም አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለፕሮጀክቱ ትግበራ የገንዘብ ድጋፍ የተገኘው (DANDA) ከተባለ የዴንማርክ አለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት ሲሆን፤ በማማከር፣ በፕሮጀክት ቀረጻ እና ክትትል በማድረግ ረገድ ደግሞ ኤስ.ኦ.ኤስ ዴንማርክ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ድርጅቱ ይህንን ፕሮጀክት ሲያዘጋጅ አገሪቱ ውስጥ ያለውን ውስብስብ የወጣቶችን ችግሮች በጥልቀት በመረዳት የበኩሉን አስተዎጽኦ ለማድረግ እንደሆነም የገለፁት ሳህለማርያም፤ ፕሮጀክቱ እንደመጀመሪያ በ3 ዓመት ከ6 ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙንም አስረድተዋል።ፕሮጀክቱ ሦስት ንዑስ አበይት አላማዎች ያሉት ሲሆን፤ እነርሱም ከአማራጭ እንክብካቤ የወጡትን ወጣቶች የሚያግዙ ደጋፊ ፖሊሲዎችን/ ህግጋት እንዲወጡና እንዲተገበሩ ማስቻል፣ ከአማራጭ እንክብካቤ የወጡትን ወጣቶችን ፍላጎቶች እና መብቶችን ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ ማስቻል እንዲሁም ከአማራጭ እንክብካቤ የወጡ ወጣቶች መብቶቻቸውን የሚጠይቁ እንዲሁም በማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከተመደበው 95 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ውስጥ፤ ወደ 88 ነጥብ 5 በመቶ (84 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር) የሚጠጋው ቀጥታ ለፕሮግራም ማስፈጸሚያ የምውል ሲሆን፤ ቀሪው 11 ነጥብ 55 (11 ሚሊየን ብር) ለተለያዪ አስተዳደራዊ ወጪዎች እንደሚውልም ዋና ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።ኤስ.ኦ.ኤስ የሕፃናት መንደሮች እ.ኤ.አ በ1949 የተሰረተ ዓለም-አቀፍ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ኢትዮጵያዊያን አቆጣጠር በ1967 በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የነበረውን ድርቅ እና ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል የተለያዩ ክፍሎች የሚኖሩ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችን ሰብስቦ የሚያሳድግበትን የህፃናት መንደር በመቀሌ ከተማ በማቋቋም ሥራውን አንድ ብሎ ጀምሯል።

በአገራችን በይፋ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ላለፋት 47 ዓመታት በስድስት ክልሎች ማለትም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሀረር፣ ሶማሊ፣ ደቡብ እና ትግራይ ክልሎች እንዲሁም በኹለቱ የራስ አገዝ የከተማ መስተዳደሮች በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሕፃናት እና ወጣቶችን የተለያዮ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

እነዚህም ፕሮጀክቶች በህፃናት እና ወጣቶቹ እድገትና እንክብካቤ፣ በጤና፤ በትምህርት፣ በመጠለያ፣ በምግብና ሥነምግብ እንዲሁም በሥነልቦና ድጋፍ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ናቸው፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply