ሬድዋን ሁሴን የደህንነት መስሪያ ቤትን እንዲመሩ ተሾሙ

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎትን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ ተሾሙ። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ትዕግስት ሃሚድ፤ ወደ ዋና ዳይሬክተር ከፍ ያደረጋቸውን ሹመት አግኝተዋል።

ለሁለቱ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ዛሬ ሐሙስ ጥር 30፤ 2016 ሹመቱን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሹመት ከመስጠታቸው አስቀድሞ፤ ዛሬ ረፋዱን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሌሎች ሁለት ሚኒስትሮችን ሹመቶችን ለፓርላማ አቅርበው አጸድቀው ነበር።

በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው የሰሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። እርሳቸውን እንዲተኩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙት ሬድዋን ሁሴን፤ ላለፈው ሁለት ዓመት ከስምንት ወር የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል።

ሬድዋን ወደ አማካሪነት ከመዘዋወራቸው በፊት፤ ከታህሳስ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ለሚጠጋ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ነበሩ። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የስልጣን ዘመን በአጭር ጊዜያት ውስጥ በርካታ ሹመቶችን ካገኙ ባለስልጣናት አንዱ የሆኑት ሬድዋን፤ በኢትዮጵያ ጎረቤት ኤርትራ እና በአየርላንድ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)    

Source: Link to the Post

Leave a Reply