ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይልን ለማገዝ የተሰለፈው የአገር መከላከያ ሠራዊትን ጎበኙ

ሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ አሸባሪውን አልሸባብ ለመደምስ ከሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ጋር የተቀላቀለውን የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።

አሸባሪውን የአልሸባብ ታጣቂዎችን እየደመሰሰ የሚገኘውን የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ለማገዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት ዘመቻውን መቀላቀሉን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ሰሞኑን “አቶ” በሚባለው ቦታ ወደ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ሾልኮ የገባው የአሸባሪው የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን “ሁልሁል” በሚባል ንዑስ ቀበሌ ከተከበበ በኋላ ሙሉ ለሙሉ መደምሰሱን የክልሉ መንግስት የፀጥታ ምክር ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድም በአሸባሪው አልሸባብ ቡድን ላይ ከተደረገው ኦፕሬሽን በድል የተመለሰውን የክልሉ ልዩ ኃይል ሰራዊትን ለሌላ ግዳጅ ወደ አገሪቱ ድንበር በትናትናው ዕለት አሸኛኘት አድርገዋል።

ባለፉት 3 ቀናት ድንበር አልፎ የገባው የአሸባሪው አልሸባብ ታጣቂ ቡድን ከ100 በላይ አባላት ሲገደሉ፤ ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ 13 ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውም ተገልጿል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply