ሮይተርስ የዜና አውታር የኢትዮጵያ ፀጥታ ሀይሎች የፎቶግራፍ ባለሙያዬን ያለአግባብ አስረውብኛል ሲል ምሬቱን ገለፀ፡፡

ኩመራ ገመቹ የተባለው የሮይተርስ ፎቶግራፍ ባለሙያ ባለፈው ሳምንት በቤቱ ሳለ የፀጥታ ሀይሎች  በቁጥጥር ስር እንዳዋሉት የዜና አውታሩ አስታውቋል፡፡ባለፈው ሀሙስ 10 የፌደራል ፖሊስ አባላት ባለሙያውን በቤተሰቦቹ ፊት ለፊት እጆቹ ላይ ካቴና አስገብተው አስርው ወስደውታል ሲልም ከስሷል፡፡

ሮይተርስ ትናንት ሰኞ ባወጣው ዘገባ ባለሙያው ለምን እንደታሰረ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ቢጠይቅም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለ አስታውቋል፡፡የዜና አውታሩ ዋና አዘጋጅ ስቴፈን አድለር እንዳሉት ኩመራ ባለፉት አስር ዓመታት በሮይተርስ የዜና አውታር ነፃ፣ ገለልተኛ አድሏዊ ባልሆነ መልኩ ሲሰራ ነበር፡፡

የኩመራ የስራ ዘመናት ሙያዊ ብቃቱንና ወገንተኛ አለመሆኑን ያሳየበት ስለመሆኑ ምስክር ናቸው፤ እስሩም ምንም መሠረት እንደሌለው ተገንዝበናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ጋዜጠኞች ሳይፈሩ፣ ማስፈራራትና ጉዳት ሳይደርስባቸው እንዲዘግቡ ሊፈቀድላቸው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ባለፈው አርብ ፍርድ ቤት የቀረበው ኩመራ አስራ አራት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንደተሠጠውም ተዘግቧል፡፡ስለጉዳዩ ለማጣራት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሙከራ ያደረገው አሐዱ ባለሙያው በኮሚሽኑ እንዳልታሰረ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ይህንን በመያዝ የፌደራል ፖሊስን የጠየቀው አሐዱ ለጊዜው ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ 

*************************************************************************************

ዘጋቢ፡ዩሐንስ አሰፋ

ቀን 20/04/2013

Source: Link to the Post

Leave a Reply