ሰሞኑን በድንገት ህይወቱ ያለፈው ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ባደገባት ደብረታቦር ከተማ አጼ ቴዎድሮስ አደባባይ ሽኝት ተደረገለት! መስከረም 28 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ ባህርዳር የመ…

ሰሞኑን በድንገት ህይወቱ ያለፈው ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ባደገባት ደብረታቦር ከተማ አጼ ቴዎድሮስ አደባባይ ሽኝት ተደረገለት! መስከረም 28 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ ባህርዳር የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ዘመድ አዝማድ ጓደኞቹ፣ የከተማዋ እና አካባቢው ማህበረሰብ በተገኙበት ሽንት ተደርጎለታል፡፡ በሽኝቱ ላይ በአካባቢ ባህል ልቅሶ፣ የሀይማኖት አባቶች ፍታት እና ድምጻዊዩን የሚያወድሱ የግጥም ስራዎች ቀርበዋል፡፡ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደርም በድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ስም መንገድ ሰይሞለታል፡፡ በድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ሽኝት ላይ የተገኙት የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባሻ እንግዳው እንዳሉት በድምጻዊ ማዲንጎ ሞት የደብረታቦር እና የሀገራችን ህዝቦች የባዶነት ስሜት እንደተሰማቸው ገልጸው ያላዜመበት ጉዳይ አለመኖሩን እና ለሀገሩ መከራና ደስታም ብዙ ስራዎችን ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡ ለከተማችን እድገትም ፈር ቀዳጅ ሚናውን መጫዎቱን ጠቅሰው በመሞቱም የደረሰብን ሀዘን ጥልቅ ነው ብለዋል፡፡ ስራውን ወዳድ እና አክባሪ መሆኑንም ተናግረው ለብዙ ወጣቶችም አርአያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሌላው የማህበረሰብ ክፍልም እንደ ማዲንጎ ስሙን ከመቃብር በላይ የሚያስጠሩ ጥሩ ነገሮችን ሰርቶ ማለፍ እንዳለበት አቶ ባሻ አስገንዝበዋል፡፡ የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ እንደተናገሩት በድምጻዊ ማዲንጎ ድንገተኛ ሞት የተሰማን ሀዘን ጥልቅ እና መሪር ነው ብለዋል፡፡ ማዲንጎ እውቀቱን እና ጥበቡን ለወገኑ እና ለሀገሩ ያበረከተ ጀግና የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሀሳቡን እና ስራውን በመቀበል እንደእሱ አይነት የጥበብ ፈርጦች መፈጠር እንዳለባቸውም አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡ በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ ከተገኙት የስራ አጋሮቹ መካከል አርቲስት አብርሃም ወልዴ እና ድምጻዊ ብርሃኑ ተዘራ እንደገለጹት ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ለሚሰራቸው ስራዎች ተጨንቆ እና ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ እንደነበር አውስተው በህዝቡ ያለው ተቀባይነት እና ተወዳጅነትም ታይቷል ብለዋል፡፡ በሙያው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን እና ለማህበረሰቡም ትልቅ ፍቅር መኖሩን ተናግረው በጓደኞቹም ተወዳጅ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡ ሀዘኑ ከባድ ቢሆንም የሰራቸው ጥሩ ስራዎች ህያው ሆነው ሲያስተውሱት ይኖራሉ ብለዋል፡፡ የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ወንድም ድምጻዊ ያሬድ አፈወርቅ እንደተናገረው ወንድሙ ለደብረታቦር እና አካባቢው ህዝብ ትልቅ አክብሮት እንደነበረው አውስቶ የሽኝት ፕሮግራሙን ማህበረሰቡ ለሱ ያለውን ቦታ የሚያሳይ ነው ብሏል፡፡ ከጎናቸው በመሆን የሃዘናቸው ተካፋይ ለሆነው መላው ህዝብም ምስጋና አቅርቧል፡፡ በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የደቡብ ጎንደር ዞን ሀገረስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀሰዩማን ቀሲስ ምህረት ሞላ እንዳሉት ማዲንጎ አፈወርቅ ለወገን እና ለሀገር የቆመ ብዙ ደሃዎችን የሸፈነ ታላቅ ድምጻዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳን በትንሽ እድሜው በሞት ቢለየንም በሰራቸው ድንቅ ስራዎች ዘላለም ሲታወስ እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡ ሀገራችን ከፍ ያደረገ እና ለህዝብ አንድነት የቆመ እንደነበርም አውስተው ሁላችንም ባለንበት ጊዜ ጥሩ ስራወችን መስራት እንዳለብንም ሊቀስዩማን ቀሲስ ምህረት አስገንዘበዋል፡፡ በድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ቤተሰቦች መኖሪያ ቤትም ስንብት እና ማስተዛዘኑ ይቀጥላል፡፡ ዘገባው የደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ነው ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply