ሰቆቃወ ኢትዮጵያ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ቆቃ ኢትዮጵያ

“የማለቅሰው ስለነዚህ ነገሮች ነው  ዐይኖቼ በእንባ ተሞልተዋል  ሊያጽናናኝ የቀረበ፤ መንፈሴን ሊያረጋጋ የሞከረ ማንም የለም ፤ ጠላት በርትቷልና ልጆቼ ተጨንቀዋል።  ካህናና ሽማግሌዎቼ ምግብ ሲፈልጉ በከተማይቱ አለቁ ።… በውጭ ሰይፍ ይፈጃል በቤትም ውስጥ ሞት አለ  ሰዎች የሥቃይ ልቅሶዬን ሰሙ  የሚያጽናናኝ ግን ማንም የለም” ።… ዐይኔ በልቅሶ ደከመ  ነፍሴ በውስጤ ተሰቃየች  ልቤ በሐዘን ፈሰሰች፤ በከተማይቱም መንገዶች ላይ ሕዝቤ ተደምስሰዋልና  ልጆና ሕፃናት በየመንገዱ ወድቀዋልና ”። ሰቆ፡ ፩፥፲፮-፳፪

ወገኖቼ ዘንድሮ የማቀርብላችሁ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ የሚለውን የተለመደ መልካም የደስታ ምኞት አይደለም፤ ሀገሬ አርባ ዘመናትን ዘልቃ የአለችበትን ሰቆቃወ የኢትጵያን ለቅሶ ይሆናል።

“ራኄል ስለ ልጆቹ አለቀሰች ፤ መጽናናትም አልቻለችም ልጆቿ ሁሉ አልቀዋልና”። ማቴ ፪፥፲፮-፲፰፤

የራኄል ለቅሶ በአንድ ወቅት የተፈጸመ ነው ። የኢትዮጵያ ለቅሶ ሰባት ሱበኤያት አስቆጥሮ ወደ ስምንተኛ ሱባኤ (ግማሽ ምዕት ዓመት) ተሸጋግሯል (እየተሸጋገረ ነው)። የራኄል እንባዋ (ሰቆቃዋ) ላላጠባቻቸውና ለአላቀፈቻቸው ሕፃናት ነው። የኢትዮጵያ ሰቆቃ ግን ለየት ይላል፤ ወልዳ፤ አጥብታ፤ አሳድጋና አስተምራ ለቁም ነገር የደረሱ ሠርግ የተደገሰላቸው ሙሽሮች ናቸው።

ራኄል የተፈጸመባት ግፍ በባዕድ ሀገር ነው ። ኢትዮጵያ ግን የተፈጸመባትና እየተፈጸመባት የአለው በገዛ ምድሯ ነው ። በራኄል ላይ ይህ ግፍ የተፈጸመበት ዘመን ፤ ዘመነ-ፍዳ ፣ ዘመነ-ኩነኔ ሲሆን መመርያውም ሕገ-አራዊት ነበር። ኢትዮጵያ ግን የአለችበት ዘመን ዓመተ ምሕረት ሲሆን የምትመራባቸው ሕጎች ሀ/ ሕገ ርትዕ (ሕገ ኦሪት) ለ/ የፍቅር ሕግ (ሕገ ወንጌል) ሕገ ትሩፋት) ሐ/ ዓለም አቀፍ ሕግ ናቸው። ስለዚህ ዘመን ከዘመን ጋር ፣ ሕግ ከሕግ ጋር ሲነጻጸር ፣ በዚህ በሃያ አንደኛው ምዕት ዓመት ኢትዮጵያ ላይ የደረሰው ሰቆቃ ፤ እየተፈጸመባት የአለው ግፍ በሰው አእምሮ ሊገመት አይቻልም።

ራኄል ይህ ዓይነቱ ግፍ የተፈጸመባት ለአንድ ጊዜ ብቻ፤ ወገኖቿ በአልሆኑ ባዕዳን ነው ። ኢትዮጵያ ግን በተደጋጋሚ፥ ደርግ ለ፲፯ ዓመታት ቀይ ሽብር ነጭ ሽብርና የቀይ ኮከብ ዘመቻ በማለት፤ ኢሕአዲግ ደግሞ ዲሞክራሲ ፤ ልማት ኅዳሴና የመሳሰለውን ምክንያት በመስጠት ፤ ባዕድ ከውጪ ሳይመጣ ፣ በገዛ ልጆቿ ታነባለች ። ለአራት አስሮች የኀዘን ማቋን አላወለቀችም ፤ ሰቆቃዋም አላቋረጠም ። ራኄል ጩኸት ያሰማችው (አቤቱታዋን ያቀረበችው) ለለመነው የሚሰጥ ፣ ለፈለገው የሚገኝ ፣ በሩን በጸሎት ለአንኳኳ የሚከፍት ፣ ጩኸትን ሁሉ ወደሚሰማው አምላኳ ነው “ለምኑ ይሰጣችኋል ፈልጉ ታገኛላችሁ ደጅ ጽፉ ይከፈትላችኋል” ተብሎ በዘመነ ሐዲስ ተጽፋልና። ማቴ ፯፥፯። ኢትዮጵያ ግን “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል በአለማመን አዚም ተሽፍና ፣ በዘመናቸው ኃያላን የተባሉ የግብፅ ፣ የባቢሎን ፣ የግሪክንና የሮም አወዳደቅን ረስታ፤ በዚህ ዘመን ኃያላን ለተባሉ መንግሥታት ጩኸቷን ታሰማለች (እያሰማች) ነው። “በገዢዎች አትታመኑ ፤ ማዳን በማይችሉ በሥጋ ለባሾችም አትመኩ ። መንፈሳቸው ትወጣለች ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ ፤ ያን ጊዜ ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል ። መዝ ፻፵፮፥፫-፱ ፤ የሚለውን የቀደሙ አባቶቿ የተጓዙበትን ዘነጋች ፣ ቸል አለች። በጥንቱ ዘመን የኢትዮጵያ ፓርላማ ስብሰባው ሲጀመርና ሲፈጸም በጸሎት ነበር። ለዚሁም ጸሎቱን የሚመሩ (የሚያሳርጉ) በሃይማኖት ተቋማት የተመደቡ ነበሩ። በዚህ ዘመን እንኳን ይህ ሊደረግ ይቅርና በአንድ ወቅት የግል የፓርላማ ተመራጭ የሆኑት አቶ ግርማ (አንድ ተወካይ) በስብሳባው ወቅት የእግዚአብሔርን ሰም ሲጠሩ የሹፈት ሳቅ ካፈ ጉባኤ ካአባ ዱላ የጀመረው ፣ ቤቱ በሙሉ እንቁላል መጣል እንደ ጀመሩ የቤት አእዋፍ ሲያስካኩ ተደምጧል። ለዚሁም ዋጋ ስለሚከፍሉብት የእናት ኢትዮጵያ ሰቆቃዋ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ይዘልቃል። ለምን ቢባል ዛሬ የአሉት የልጆቿ ዝርክርክነትና እምነት አልባነት ጨካኝነት ስግብግብነትና ተንኮል ትንቢት ይናገራል። ”እሾክ ለአጣሪው ሥራ ለሠሪው” ፣ “በሠፈሩት መሠፈር” የሚሉት ሕዝባዊ አባባሎች ተግባራዊነታቸው ያለፉት ድርጊቶችና ታሪኮች ምሥክሮች ናቸውና። “ከጥላቻችሁ የተነሣ በእነሱ ላይ በገለጣችሁት ቁጣና ቅናት ልክ እፈርድባችኋለሁ፤ በእናንተም ላይ በምፈርድት ጊዜ ማንነቴ በእነርሱ መካከል እንዲታወቅ አደርጋለሁ”። ሕዝ ፴፭፦፲፩-፲፪፤

ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በአለንበት ሁሉ የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል ከእናታችን ጋር በሰቆቃ ልናከብረው ግድ ይለናል።

“የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ በሆነች ጊዜ ስለ ተደሰትክ እኔም እንዲህ አደርግብሃለሁ” ሕዝ ፴፭፥፲፭።

ዛሬ የዘመናችን መሣፍንት አይደለም የትንሣኤን በዓል፣ በአዘቦቱ ቀን ምክንያት እየፈጠሩ በአለማቋረጥ አሸሼ ገዳሜ የሚሉ  ብዙ ናቸው። እነዚህንም  ክፍሎች በብዙኀን መገናኛ (የሚድያ) መስኮቶች ዘወትር እናያቸዋለን ፣ እንሰማቸዋለን። “እግዚአብሔር ዘፈን ሲያምረው … ያጠግባል” የሚለው አባባል ይሆን? ብየ አሰብኩ፤ ግን አይደለም፤ ከተጨፈጨፉትና ከሚሰቃዩት ልጆቿ ክፊሉ ከእዛ ወገን ናቸውና። በኀዘን ላይ ተቀምጣ፤ ሰቆቃው እያሰማች፤ ወንድሞቻቸው እህቶቻቸው ህፃናቱ ሳይቀሩ እሬሳቸው ቀባሪ እስከ ማጣት ደርሷል። መለስ ብለን የታሪክ ማኅደር ስንዳስስ ፣ ቀባሪ የአገኘው እሬሳ የገቢ ምንጭ የሆነበት ዘመንን አይተናል። ለ፲፯ ዓመታት ደርግና የደርግ አጫፋሪዎች ይህን አድርገዋል። ዛሬም የወይኔ (የኢሕአዲግ) አጫፋሪዎች ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል እየደጋገሙት ነው። የደርግ አጭፋሪዎች ሌላው ቀን አንሷቸው በዐቢይ ጾም ፍሪዳ እያረዱ ውስኪ እያንቆረቆሩ ጨፍረዋል። የኢሕአዲግ አጫፋሪዎችም ቀኑ አልበቃ ብልዋቸው ሌሊቱን ያነጋሉ። ነቢዩ ሕዝቅኤል እንደተነበየው ደርግ መሣርያ ይዞ ዳቦ ለመነ። “እስመ ኩሉ ጾሮ ይጸውር ነውና”ኢሕአዲግ አጫፋሪዎችም ከዚህ የከፋ እንደሚጠብቃቸው የእግዚአብሔር ቃል አይዋሽም። ከዚህ ለመዳን ዛሬ ጀንበሯ እያቆለቆለቸ ነው። ሳትጠልቅ ንስሐ ግቡ። ወደ ኀሊናችሁ ተመለሱ። የእግዚአብሔርን ቃል ባትቀበሉ ከፊታችሁ የአጻፋ ምት የተመቱትን ደርግን፤ ገዳፊን ፣ ሙባርቅንና ሳዳምን ተመልከቱ፤ ከእነሱ ተማሩ፤ ድንገት አለን አለን ሲሉ ጀንበር ጠልቃባቸዋለችና።

“ዮም ፍስሐ ኮነ” በማለት አንገርጋሪው አይመራ (አይመልጠን)።

ካህናቱ በእርሱ ፈንታ መዋሥኢቱን ይተኩ። የዘንድሮውን የትንሣኤ በአላችንን ከበሮ በመደለቅ የሚደረገው ፈጠዝያ ያቁም፤ ለሙታን የሚደረገው ጸሎት ይድረስ። መንጋውን እንዲጠብቁ አደራውን የተቀበሉ ጳጳሳት ፣ ቆሞሳት ካህናት ፣ ሰባክያን ፣ ማኅበራትና መዘምራን እንዲጠብቁት አደራ የሰጠቻቸው መንጋው የአላግባብ ሲጨፈጭፍ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል። ጥቅማጥቅሙን ማጋበስ የዘወትር ተግባራቸው አድርገዋል። እናት ኢትዮጵያ በኀዘን ተቆራምዳ ፣ የኀዘን ከል ለብሳ ፣ ለለቅሶዋ የደረሰ የለም። የ፲፯ ዓመታት የደርግ ቅልብ ሆነው አሳልፈዋል፤ አባታቸውን ፓትርያሪኩን ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል። ዛሬም በጣት ከሚቆጠሩ በቀር አብዛኛው የኢሕአዲግ አጫፋሪ ሆነው፤ አብረው ተባባሪ በመሆን እይፈነጠዙ ፣ እየገደሉና እያስገደሉ  ናቸው። “እራሳቸውን ብቻ ለሚንከባከቡ እረኞች ወዮላቸው፤ እረኞች መንጋውን መንክባከብ (ማሰማራት) አልነበረባቸውምን? ጮማውን ትበላላችሁ ፤ ከጠጉሩ የተሠራውን ሱፍ ትለብሳላችሁ፤ የሰባውን አረዳችሁ፤ ነገር ግን መንጋውን አትንከባከቡም።.. የባዘኑትን አልመለሳችሁም፤ የጠፉትን አልፈለጋችሁም፤ በግፍና በጭካኔ ገዛችኋቸው። ሕዝ ፴፬፥፩–፮፤ በዚህ ዘመን እንደዚህ መንጋውን እየበደልን  ለአለን ጳጳስት ፣ ቆሞሳት ፣ ካህናትና ሰባክያን ወዮልን፤ ወዮታ አለብን፤ አደራ በላ ሆነናል፤ ኃላፊነታችንን አልተወጣንም። ከሚመጣው ፍርድ ለመዳን ንስሐ እንግባ። “እናንተ ኃጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ኃሣብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁ ወደ ትካዜ ይለወጥ” ያዕ ፬፥፯-፲።

ወገኖቼ የዘንድሮውን በዓል በሰቆቃው እንድናከብር የጠየቅሁት ለሁለት ምክንያት ነው። ፩/ አሁን እይተፈጸመ ስላለው ፪/ ሳንጠቀምበት የአጣነው ዕድል እንዳይደገም ለማሳሰብ ነው።

፩/    አሁን እየተፈጸመ ያለው፤

“የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮሃል፤ ደሙን ከእጅህ እፈልጋለሁ” ያለ እግዚአብሔር ፣ በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር የአመጽና የግፍ ምት ንጽሐ-ጠባይ ያላደፈባቸው፤ ሕፃናት በጠራራ ፀሐይ በከተሞች መካከል ደማቸው እንደ ጎርፍ ፈሷል። በአሲንባ ተራራ ፣ በደደቢት ዱር (በርሐ) በርካታ ምሁራን ፣ በርካታ ጀግኖች እርስ በራሳቸው በመገዳደል የአራዊት የአእዋፍ ምግብ ሆነው ቀርተዋል።

እምዬ ኢትዮጵያ ሰቆቃዋ ያኔ ሀ ብሎ ጀመረ ። በመቀጠልም ኢሕአዲግ በመንገድ ላይ ጉዞው እያፈረሰ ፣ እያቃጠለና እየገደለ በትረ መንግሥቱን ጨብጧል (መሐል ከተማ ገብቷል)። በትረ መንግሥቱን ከጨበጠ በኋላ በጎንደር በአደባባይ ኢየሱስና በአዲስ አበባ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በአውደ ምሕረቱ በቤተ መቅደሱ በግፍ እንደተገደለው እንደ ዘካርያስ የንጽሐን ደም በከንቱ ፈሷል። ትናንትና በወልድያ በጥምቀት በዓል አክባሪዎች ላይ፣ እንዲሁም በሞያሌ የየዕለት ተግባራችውን በሰላም በመፈጸም ባሉት ላይ ጭፍጨፋ ተፈጽሞ ደማቸው በከንቱ ፈሷል።

ለአንድ ዘካርያስ ደም ጩኸት መልስ ከሰጠ ፣ የዚህን ያህል ደም በከንቱ ሲፈስ መልሱ (አጻፋው) ምን ይሆን? ማቴ ፳፫፥፴፪-፴፮። ልብሱን አውልቆ በቀን በሕዝብ መካካል የሚመላለስ የለም፤ ቢሆንም የአእምሮ የጤና መታወክ ያለበት ሰው አልፎ አልፎ ሲያደርገው ይታያል። ዛሬ ግን የኢትዮጳያ ሕዝብ ከሕፃን እስከ አረጋዊ ፣ ከመሪ እስክ ተመሪ ፣ ከጳጳስ እስከ አጻዌ ኆኅት፤ እርቃኑን ይመላለሳል። ሁሉም አንድ ስለሆነ መተፋፈር ጠፍቷል። ያ ማለት እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠውን የአምልኮት ልብሰ ፀጋ አውልቆ መጣሉን ያመለክታል። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፲፪፤ የኢትዮጵያ አላቋርጥ ያለው ሰቆቃዋ ልጆቿ ይህንን ፀጋ ማጣታቸው ነው። አሁንም በአለማቋረጥ ሰቆቃው ፣ ዋይታው ፣ ክህደቱና ግድያው በዚሁ ትውልድ ላይ ያቁም፤ በሚቀጥለው ትውልድ ላይ አይተላለፍ፤ አይደገም፤ በማለት እጆቿን ዘርግታ ታነባለች። መዝ ፷፯፥፴፩፤

፪/    ሳንጠቀምበት ያሳለፍነው ዕድል ዛሬም እንዳይደገም እንጠንቀቅ፤

ኢትዮጵያ በ19ኛ መቶ ክፍለ ዘመን መጀመርያ መሣፍንት ልጆቿ እርስ በርሳቸው ተከፋፍለው ፣ እርስ በርሳቸው ጦር ተማዘዙ። የአንድ እናት ልጆች እርስ በርሳቸው ተዋደቁ፤ “የገደለው ባልሽ ፣ የሞተው ወንድምሽ ፣ ለቅሶሽ ቅጥ አጣ..” የአለው ሆነና የልቅሶ ማቅ ለበሰች፤  እሷነቷንም አሳነሱት፤ በኀዘን ተኮራመተች። የደረሰባትን የልጅ ኀዘን ጎረቤቶቼ ሰሙ። አይዞሽ የሚላት ፣ ሊያጽናንናት የሞከረ የለም። እንዳውም የልጆቿ እርስ በራስ መለያት ሠርግና ምላሽ ሆነላችው። ድንበር ለመግፋት ፣ እርስት ለማስፋት ዕድል ተክፍቶላቸዋልና፤ እርሷም ለልጆቿ፦ ልጆቼ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደሚባለው በኅብረት ኑሩ፤ ቅዱሳትመጻሕፍትም በየክፍላቸው ፍቅርን ፣ አንድነትን  ኅብረትን ያውጃሉ፤ ሳይንሱም ከዚህ የተለየ አይደለም። የኦክስጅንና የሃይድሮጂን አንድነት (ውኅደት) ታጥበን የምንነጻበትን ፣ ጠጥተነው የምንካበትን ውኃ አስገኝቷል። እባካችሁ ልጆቼ  የኀዘን ማቄን አውልቃችሁ ጣሉልኝ ብላ ተማጸነች። ዳዊት ታሞ የቤተ ልሔምን ውኃ እንደተመኘና ባለሟሎቹ ከጠላት ጋር ተቋቁመው እንደአመጡለት ታሪክ ይነግረናል። የእምዬ የኢትዮጵያ ልጆችም ‘የማን እናት ናት ስታነባ የምትኖር’ በማለት፥ ቴዎድሮስ ተነሣ የአንድነት መሠረት ጣለ ፤ ዮሐንስ ደገመ ፤ ምኒልክ ሠለሰ፣ የአድዋን ድል አስመዘገበ፤ ኃይለ ሥላሴ የቀይ ባሕርን ድንበር በማስመለስ ሙሉ ኢትዮጵያን አስረከበ። እናት ኢትዮጵያ የኀዘን ማቋ ወልቆ ፣ እንባዋ ታብሶ ለምዕት ዓመታት እፎይ ብላ ኖረች።

መንግሥቱ ተነሳ፤ “ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን መፈክር ለውጦ ሀገሪቷን አኬልዴማ (የደም ምድር አደረጋት)፤ እናት ኢትዮጵያ እንደገና የኀዘን ማቅ ለበሰች፤ በሰቆቃ ተሞላች። ያን ጊዜ የልጆቿ አንድነት ተናጋ፤ ኢሕአዲግ ተረከበ፤ ይባስ ብሎ በዘር ከፋፈለው፤ ዘመነ መሣፍንትን መልሶ እንዲመጣ መንገዱን አዘጋጀ፤ አሁን የአለነው እዚያ ዋዜማ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሦስት ጊዜ የመጣለትን ዕድል ሳይጠቀምበት በከንቱ አባክኖታል ፤ ዛሬ ደግሞ አራተኛው ዕድል መጥቶለት ነጣቂዎች ሊቀሙት እያደቡ ናቸው። ዕድሎቹ ምን ነበሩ? በማን? እንዴት ተነጠቁ?

፩/      በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም. በብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ የተጀመረው እንቅስቃሴ ራእይ የሌለው ፣ ራእይ ሰጪውን ያላስቀደመ፤ ጥናት የጎደለው፤ ኅብረትን ያላካተተ፤ “ባወጣ ያውጣ” በማለት በስሜት ፣ በክዳት፤ በአድማና በመግደል ተጀመረ፤ ወዲያው በመገዳደል ተጠናቀቀ።

፪/      በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. በተማሪዎች እንዲሁም “ምሁራን” በተባሉት ግፊት አብዮት ፈነዳ። በወቅቱ የነበሩት ምሁራንና ተማሪዎች፣ የማርክስ ፣ የኤንግልስ ፣ የማኦንና የሌኒኒን መጻሕፍት ያነበቡና በዚያም የተጠመቁ ነበሩ። የሚጽፉትና የሚናገሩት የቻይናንና የራሽያን አብዮት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ነበር። ይህንኑ ለማምጣትገና ከጅምሩ ኢሕአፓ ፣ መኢሶን ፣ ሰደድ ፣ ኢጨአት ፤ በመባል ተከፋፍፈሉ። እርስ በርስ በቃላትና በጥይት መደባደብ ጀመሩ። በግርግሩ መሐል የታጠቀው ክፍል ለኢትዮጵያ ሕዝብ የመጣውን ዕድል ቀምቶ ወሰደው። ለዚህ ዕድል መነጠቅ ምክንያቱ ምሁራን ተብየዎች ናቸው። ምክንያቱም የኢትዮጵያን ፓለቲካ ፣ ታሪክና የሕዝቡን ሥነ ልቡና በአለማወቃቸው የተነሳ ነው። ለትልቅ ካሚዎን የሚገጠመው ጎማ ለትንሽ መኪና መግጠም አይቻልም፤ በደጋ የሚስማማው ዛፍ ቆላ ቢትክሉት አይስማማውምና። በሀገራችንም የዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው የተፈጸመው። ትልቁ ውድቀት ደግሞ የኃይል ምንጭ ፣ የእውቀት መሠረት ፣ የኃብት ሁሉ መገኛ ፣ የግዙፉንና የረቂቁን ፈጣሪ ፣ እግዚአብሔርን አውጥቶ መጣል ነበር።

፫/      በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. የመጣው ሦስተኛው የኢትዮጵያን ሕዝብ ዕድል የጠየቀውን ቀርቶ ያልጠበቀውን አመጣ ። ኢሕአዲግ ሲመጣ ራእይ ሰጪውን ገድፎ የራሱን ራዕይ አንግቦ በዓላማ ነው። ዓላማው ወይንም ራእዩ በላይ ሲታይ መድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ያሰፈነ ሲመስል ፣ በውስጡ ግን “ክፋፍለህ ግዛ” የሚለው የቅኝ ገዢዎች ይትበኃልን ያነገበ ነበር። ይህም በዘጠና ሰባቱ ምርጫና ዛሬ በሚያደርገው እሥራትና ግድያ ለማረጋገጥ ተችሏል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሦስተኛ ጊዜ ተታለለ፤ የመጣለትን ዕድል ተነጥቆ ምድራዊ ሲኦልን እየገፋ ይገኛል።

፬/      በ፳፻ወ፰ ዓ.ም የተጀመረውና አሁንም በመካሄድ ላይ የአለው አብዮታዊ መስል ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለአራተኛ ጊዜ የተከሠተ ዕድል ነው። ይህ አራተኛው ዕድል ሲሆን የመጣው ሦስተኛው ሱባኤ ተፈጽሞ አራተኛው መገባደጃው ላይ ነው። የእናታችን ኢትዮጵያ ሰቆቃዋም ግማሽ ምዕት ዓመት ያህል አስቆጥሯል። ይህ አራተኛው ዕድል ደግሞ እንዳያመልጣቸው ማስጠንቀቂያና ምክር ለልጆቿ እንደሚከተለው ታቀርባለች።

ሀ/    ልጆቼ ለግማሽ ምዕት ዓመት ያህል ከል ለበስኩ፤ ማቅ አገለደምኩ፤ እንባየ አልቆ እዥ እዤ አልቆ ቁጹረ ገጽ ሆኛለሁ። “ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም” በማለት ለልጆቼ የመጣላቸውን ዕድል ለውጦ ያለ ስጦታው (በአልሰለጠነበት) “ወታደራዊ ደርግ” ብሎ ሥልጣኑን (በትረ መንግሥቱን) በጉልበት ተቆጣጠረ፤ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን የአስተዳደሩትን እድሜ ጠገብ ንጉሠ ነገሥቱን ገድሎ ሽንት ቤቱ ሥር ቀበረ፤ ምትክ የማይገኝላቸው ሀገሪቱ ያስተማረቻቸውን ምሁራን  ባለሥልጣኖች ያለምንም የፍርድ ቤት ውሳኔ ረሽኖ ከ፷ በላይ የሆኑትን በአንድ ጉድጓድ ቀበራቸው። ቀይ ሽብር እያለ ወጣቱን ፈጀ። የቀይ ኮከብ ዘመቻ በማለት በኤርትራ ኢትዮጵያውያን ላይ አዘመተ፤ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ አፋጃቸው። “ተፈጥሮን እንቆጣጠራለን” በማለት ፈከረ፤ ግን ኢትዮጵያውያን ምግብ አጥተው በመቶ ሺ የሚቆጠሩ በጠኔ አለቁ፤ “ኢምፔርያሊዝም ይወድማል፤ ደሙን እንዲህ እናፈሰዋለን” እያለ ፈከረ፤ ከአለው ጋር ተባበረ። ይባስ ብሎ ልጆቼን ደግሞ ለሚውጥ ዘንዶና ለተናዳፊ እባብ ዳረጋችው።

ለ/    ልጆቼ የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ለአራተኛ ጊዜ አንዳይደገም የመጣውን ዕድል ተጠቀሙበት፤ “ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር” ነውና ቴዎድሮስ መቅደላ አምባ ላይ፣ ዮሐንስ መተማ ላይ መስዋዕትነት ከፈሉልኝ፤ በእነሱ መስዋዕትነት ምኒልክ የአድዋን ድል አቀዳጀኝ፤ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ የጥንት አካሌን መልሶ ቀይ ባሕርይን አጎናጸፈኝ፣ ወደቦቼን አስረከበኝ። ልጆቼ የቀደሟችሁን ምሰሉ፤ እንባዬን አብሱልኝ፤ ማቄን አውልቁልኝ፤ “ምሁራን ነን” የምትሉ ሦስት ጊዜ የመጣውን ዕድል እኔ “ለእኔ ፣ ለእኔ ስትሉ” ባለመስማማት የተነሳ ሁሉን አጣችሁ፤ ይህ አሁንም እንዳይደገም በእግዚአብሔር አዳኝባችኋለሁ። ቄሮ፣ ፋኖ የተባላችሁ ልጆቼ የአለፈውን ታሪክ እንዳትደግሙት እፈራለሁ፤ ነፋስ የሚገፋው ቃጠሎ ጥፋቱ በቀላል የሚገመት አይደለም። በነፋስ ፣ በእሳት ባሕርይ የአላችሁ ቄሮና ፋኖ ረጋ ብላችሁ ያለፈውን የእትዮጵያን ሰቆቃ ተመልከቱ። በእድሜ የቀደሟችሁን፣ በትምህርት የሚበልጧችሁን ፣ ራእዩ የተሰጣቸውን ፣ የአምልኮት መልክ የአላቸውን አዳምጡ። ይህንን እውን ከአደረጋችሁ የእኔን ትንሣኤ ታበሥራላችሁ። ከዚያ በኋላ “ዮም ፍሥሐ ኮነ” ብላችሁ የጌታየን ፣ የአዳኘን ፣ የአምላኬንና የንጉሤን ትንሣኤ ልታከብሩ ትችላላችሁ። ለዚያ ያብቃኝ፤ ያብቃችሁ፤ አሜን።

                                                                  “ወስብሐት ለእግዚአብሔር”  

ከአ/ካ

ሊቀ ማእመራን ቀሲስ ዶክተር አማረ ካሣዬ

በዝርወት ላይ የምትገኝ የርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ዋሽንግተን ፣ ዲሲ

መጋቢት፴ ቀን ፳፻ወ፲ ዓ.ም. (04/08/2018)

ፀሐፊውን ለማግኘት

Leave a Reply