ሰበር ዜና! መኖሪያ ቤታቸው በኦሮሚያ ክልል መንግስት የፈረሰባቸው ሰዎች እራሳቸውን አጠፉ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ … የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ አከባቢዎች መኖሪያ ቤታቸው በኦሮሚያ ክልል መንግስት የፈረሰባቸው ሰዎች እራሳቸውን ማጥፋታቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል። በቅርቡ በተመሰረተው እና ተጠሪነቱ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ነው በተባለው ሸገር ከተማ ስር በተካተቱ ስድስት ክፍላተ ከተሞች ህገ ወጥ ናቸው በሚል ማንነትን በለየ መልኩ የአማራ ተወላጆች መኖሪያ ቤት እየፈረሰ ይገኛል። በሰበታ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ሱሉልታ እና ገላን የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ያለ ምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ መኖሪያ ቤታቸው ፈርሶባቸው ጎዳና ላይ ወድቀዋል። የክልሉ ልዩ ኃይል በሚያጅበው ግብረ ኃይል መኖሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸው እና መውደቂያ ያጡ ሰዎች ባደረባቸው የአዕምሮ ጭንቀት እራሳቸውን ማጥፋታቸውን ነው የአይን እማኞች አረጋግጠዋል። ተበድረው እና ያላቸውን ጥሪት አሟጠው የሰሩት መኖሪያ ቤት ሲፈርስ ተስፋ በመቁረጥ በገመድ በመታነቅ እና መርዝ በመጠጣት በሱሉልታ አካባቢ እስከ አሁን የታወቁ ሁለት ሰዎች እራሳቸውን ማጥፋታቸውን ነው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች የተናገሩት። ቤተሰቦቻቸውን የሚያስጠጉበት እና የሚያስጠልሉበት ያጡ በርካታ ሰዎች በእዕምሮ ጭንቀት እራሳቸውን ስተው ሆስፒታል መወሰዳቸውም ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ መኖሪያ ቤታቸው በመፍረሱ እና የሚጠለሉበት በማጣታቸው በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ቀርተዋል። በለገጣፎ ለገዳዲ መኖሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሌላኛው ተጎጂ፣ “አዲስ ያሰራሁት መኖሪያ ቤቴ ፈርሷል፣ ከባለቤቴ ጋር ለአመታት ጥረን ግረን ያፈራነው ሀብት ንብረት በአፍራሽ ግብረ ኃይሉ ወድሟል ስለዚህ ብቸኛ አማራጫችን እራስን ማጥፋት ሁኗል” ብለዋል። ትናንት የተሻለ ህይወት እኖር ነበር ዛሬ ግን ከነቤተሰቦቼ መጠለያ አጥቼ እየተንከራተትኩ ነው ያሉ ሲሆን በልመና ህይወት መሰማራታቸውን ጨምረው ገልፀዋል። እየተካሄደ የሚገኘው የቤት ማፍረስ ዘመቻ አሁንም መቀጠሉ የተገለፀ ሲሆን ከኦሮሞ ተወላጆች ውጭ የሌሎች ብሔር ተወላጆች መኖሪያ ቤት እንዲፈርስ ምልክት እንደተደረገበት ነዋሪዎቹ ገልፀዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናት፣ እናቶች እና አዛውንቶች የሚጠለሉበት አጥተው ጎዳና ላይ የወደቁ ሲሆን አንድ አከባቢ ተሰባስበው እንዳይገኙ በፀጥታ ኃይሎች እንዲበተኑ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል። በግሬደር ማሽን በመታገዝ መኖሪያ ቤቶችን እያፈረሰ የሚገኘውን ግብረ ኃይል የሚያጅቡት የኦሮሚያ ፀጥታ ኃይሎች ቤታችንን አናስፈርስም ባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው አይዘነጋም። ዘገባው የአማራ ድምፅ ነው።
Source: Link to the Post