
ሰበር ዜና! በአዲስ አበባ አሁንም ቀጥሏል ከተባለው መንግስታዊ አፈና ጋር በተያያዘ በሌሊት ተይዘው፣ ደብዛቸው የጠፋ ቤተሰቦች አፋልጉን ሲሉ የተማጽኖ ጥሪ አቀረቡ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ … ሀምሌ 11/2015 ዓ/ም_አዲስ አበባ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ አሁንም ቀጥሏል ከተባለው መንግስታዊ አፈና ጋር በተያያዘ በሌሊት ተይዘው፣ ደብዛቸው የጠፋ ቤተሰቦች ሀምሌ 11/2015 ለአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) አፋልጉን ሲሉ የተማጽኖ ጥሪ አቅርበዋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ድምጽ እንዲሆናቸው የጠየቁት የታፋኝ ቤተሰቦች ሶስቱም ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የካ ክ/ከተማ ነው። (1) አቶ ሙላት ከፋለ:_ በአዲስ አበባ የካ ክ/ከተማ የ02 ነዋሪ የሆነ ሲሆን በንግድ ስራ የተሰማራ መሆኑ ነው። ባለትዳር እና የልጆች አባት የሆነው አቶ ሙላት ከፋለ ሀምሌ 5/2015 ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ታፍኖ ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዱ ተሰምቷል። ቤተሰቦችም በጭንቀት ውስጥ ሆነው ከቦታ ቦታ ቢንከራተቱም እስካሁን አድራሻው የት እንደሆነ ለማወቅ አልቻሉም። (2) ብርሃኑ ንጉሴ አለሙ:_ ነዋሪነቱ በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ሲሆን በበጎ ፈቃደኝነት ተግባሩ የሚታወቅ ነው። በተለይም መንቀሳቀስ የማትችል ለሆነች ለአንዲት አቅመ ደካማ እናት በኃላፊነት ድጋፍ በማድረግ የበጎነት ስራ እየሰራ ባለበት ነው ሀምሌ 5/2015 ከሌሊቱ 5:40 ላይ ታፍኖ ወዳልታወቀ ስፍራ የተወሰደው። በሁለት መኪና የመጡ ሰዎች ከመካከላቸው አንደኛው የመከላከያ ልብስ የለበሰ እና የታጠቀ፣ ሌሎች ስድስት ሲቪሎችን ጨምሮ በድምሩ ሰባት ሆነው ወደ ቤቱ ዘልቀው በመግባት ነው አፍነው የወሰዱት ተብሏል። አሚማ ያነጋገራቸው ቤተሰቦችም ብርሃኑ ንጉሴን በቆሬ 2 ቁጥር ማዞሪያ፣ በልደታ ፖሊስ መምሪያ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ በሜክሲኮ ፌደራል ፖሊስ ማቆያ ድረስ በመመላለስ ብንፈልግም አድራሻውን የሚነግረን ስላጣን እባካችሁ አፋልጉን ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። (3) ፋሲል ጌትነት እሸቱ:_ ፋሲል ጌትነት እሸቱ ይባላል። ነዋሪነቱ በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ነው። ባለ ትዳርና አንድ ልጅ ሲሆን የአማራ ባንክ ሰራተኛ በመሆን በካሳንች አዲስ ቅርንጫፉ ባለበት በጠማማው ህንጻ ነው የሚሰራው። ሀምሌ 6/2015 ከሰዓት በኋላ አድራሻው የት እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም። ባለቤቱ፣ ጓደኞቹ እና ቤተሰቦቹ ክፉኛ ተጨንቀዋል። በካሳንችስ ፖሊስ ጣቢያ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ በሜክሲኮ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማቆያ፣ በጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ፣ አራዳ ፖሊስ መምሪያና በአካባቢው ፖሊስ ጣቢያ፣ የካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና በአካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ያለ እረፍት ስራቸውን ትተው ያፈላለጉ ቢሆንም እስካሁን የተገኘ መረጃ የለም። 28 የሚሆኑ አማራዎች ከአዲስ አበባ እና ከ ሸገር ከባለው ከተባለው ከተማ አስተዳደር ታፍነው ገላን በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ለአንድ ወር ገደማ እየሰቃዩ መቆዬታቸውን የገለጹት እነ መላክ ምሳሌ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረቡትን የሰብአዊ መብት ጥሰት አቤቱታን ተከትሎ በኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት መደረጉ እና የደረሰው ኢሰብአዊ ድርጊትም ጠበቆችንና ቤተሰብን ጭምር በእጅጉ ያሳዘነ መሆኑ ይታወቃል። አሁንም እነዚህ ደብዛቸው እንዲጠፋ የተደረጉ ወገኖች ተመሳሳይ የሆነ መንግስታዊ የአፈና ወንጀል እንዳይፈጸምባቸው ድምጽ በመሆን ረገድ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ግራ በገባቸው፣ መሄጃ በጠፋቸው እና በጨናቃቸው ቤተሰቦች ስም ተጠይቋል።
Source: Link to the Post