
ሰበር ዜና! በወልቂጤ ከተማ በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የፀጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ ሁለት ሰዎች ተገደሉ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ … የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በደቡብ ክልል ወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ለዓመታት ሊቀረፍ አልቻለም ያሉትን የንፁህ ዉሃ አቅርቦች ችግር እንዲስተካከል ለመጠየቅ አደባባይ በወጡ ነዋሪዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። በፀጥታ ኃይሎቹ ከተገደሉት በተጨማሪ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዉ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። ስማቸዉ እንዲገለፅ ያልፈለጉ የከተማ ነዋሪዎች እንደተናገሩት የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ነዋሪዎች የንፁህ ዉሃ አቅርቦት ችግር እንዲፈታ ባዶ ጀሪካን በመያዝ አደባባይ መዉጣታቸዉን ገልፀዋል። ይሁን እንጂ የክልሉ እና የዞኑ የፀጥታ ኃይሎች ሰልፈኞቹ እንዲበተኑ ተኩስ መክፈታቸውን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል። በስፍራዉ ነበርን ያሉ የአይን እማኞች እንደሚናገሩት ነዋሪዎች እና የፀጥታ ኃይሎች ከከፍተኛ ክርክር በኋላ የተኩስ እርምጃ ሲወስዱ ሁለት ሰዎች ህይወታቸዉ ሲያልፍ ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸዉ ወደተለያዩ ሆስፒታሎች ተወስደዋል ብለዋል። “አንድ ጊዜ ዉሃ ከመጣ ከአራት እስከ ስድስት ወራት ሊቆይ ይችላል” የሚሉት ነዋሪዎቹ “በተደጋጋሚ ጥያቄዎች ለሚመለከተው አካል ያቀረብን ቢሆንም ለዉሃ ግንባታ ማስጀመሪያ በሚል በከፍተኛ በጀት ጉድጓዶች ይቆፈሩና ያለ በቂ ምክንያት ይቆማሉ፤ ዛሬ በአደባባይ ነዋሪዎች በአንድ ላይ የወጡበት ምክንያት ምላሽ እንዲሰጣቸዉ ነዉ” ተብሏል። ከንፁህ ዉሃ አቅርቦች ችግር የተነሳ ለዉሃ ወለድ በሽታዎች ተጋላጭ መሆናቸዉን እንዲሁም ዉሃ ፍለጋ ጠዋት ወጥተዉ ማታ እንደሚመለሱ የዘገበው አዲስ ዘይቤ ነው።
Source: Link to the Post