ሰበር ዜና – ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተመደቡ

https://1.gravatar.com/avatar/7f09202441ad3b4b636e88820d6a7061?s=96&d=identicon&r=G

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ውሎው፣ የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደማንኛውም ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ በሊቀ ጳጳስ እንዲመራ በወሰነው የሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌ ማሻሻያ መሠረት፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን መደበ፡፡

በድንጋጌው ማሻሻያ መሠረት፣ ምልአተ ጉባኤው፣ አምስት ብፁዓን አባቶች ያሉትን አስመራጭ ኮሚቴ ሠይሟል፡፡ ኮሚቴውም፣ ሦስት ብፁዓን አባቶችን ማለትም ብፁዕ አቡነ እንጦንስን፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልንና ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን በዕጩነት አቅርቧል፡፡

በተደረገው የድምፅ አሰጣጥም፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እና ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፥ በመደበኛ ስብሰባው ከተገኙትና ድምፅ ከሰጡት 44 የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ውስጥ እኩል 17፣ 17 ድምፅ በማግኘታቸው፣ ተመራጩን ለመለየት በጸሎት የተጣለው ዕጣ ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ወጥቷል፡፡

በመኾኑም፣ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ ሀገረ ስብከታቸውን እንደያዙ፣ የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲመሩ በምልአተ ጉባኤው ተመድበዋል፡፡

ብፁዕነታቸው፣ ቀደም ባለው ልዩ ድንጋጌ መሠረት፣ በሀገረ ስብከቱ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው መሥራታቸው ይታወሳል፡፡

ለብፁዕነታቸው፣ መልካም የሥራ እና የውጤት ዘመን እንመኝላቸዋለን፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply