
ሰበር ዜና! የአማራ ድምጽ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ጌትነት አሻግሬ በፌደራል ፖሊሶች ታሰሯል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ … መጋቢት 17 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ያነጋገረው የአማራ ድምጽ ሚዲያ መስራች እና ባለቤት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እንደገለጸው በተለይም በወለጋ ጉዳይ በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ የሚገኘው ዋና አዘጋጅ (Chief editor) ጌትነት አሻግሬ በፌደራል ፖሊሶች ታስሯል። ጌትነት አሻግሬ በወለጋ የተወለደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአካባቢው በኦነጋዊያን አማካኝነት በአማራ ላይ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ስላለው የዘር ፍጅት፣ መፈናቀል፣መሳደድ እና ሁለንተናዊ ግፍ በመዘገብ ይታወቃል። እስሩ የተፈጸመው መጋቢት 17/2015 ከምሽቱ 1 ሰዓት ገደማ ሲሆን በሌሎች ሚዲያዎች ላይ ከሰሞኑ የተፈጸመውን ዝርፊያ ተከትሎ በጋዜጠኛው ቤት የነበሩ አራት የተቋሙ ኮሚፒተሮችም በፖሊሶች ስለመወሰዳቸው ተገልጧል። ጋዜጠኛ ጌትነት አሻግሬ የተወሰደው መገናኛ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ስለመሆኑ ታውቋል። አማራ ድምጽ ሚዲያ በቅርቡ ወደ ቴሌቪዥን ለመምጣት ለመምጣት በእንቅስቃሴ ላይ እንደነበር ተገልጧል። መጋቢት 17/2015 ጠዋት ላይ ጋዜጠኛ አራጋው ሲሳይ በተመሳሳይ ከቡልቡላ ወረዳ 12 በአምስት የፌደራል ፖሊሶች ታስሮ ወደ ሜክሲኮ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ መወሰዱ ይታወሳል። የማፈን፣ የማሰር እና የማዋከብ አካሄዱ ለአማራ ብሎም ለተገፉ ወገኖች ሁሉ ድምጽ የሚሆኑ አካላት እንዳይኖሩ ከመፈለግ ጭምር የመነጨ ስለመሆኑ አመላካች ነው በሚል እየተተቸ ነው። ከጋዜጠኞች በፖሊስ የሚወሰዱ የሚዲያ ግብአቶችም በአብዛኛው እየተመለሱ ባለመሆኑ በቀጥታም ይሁን በእጅ አዙር ጋዜጠኞችን የማዳከም ብሎም ከጨዋታው የማስወጣት መንገድ ተደርጎ በብዙዎች እየተወሰደ ያለ ጉዳይ ሆኗል።
Source: Link to the Post