ሰበር ዜና! የአገዛዙ ወታደሮች በምስራቅ ወለጋ ዞን አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት 37 የአማራ ተወላጆች ተገደሉ! ትናንት በስቲያ መጋቢት 06/2016 ዓ/ም እኩለ ቀን ገደ…

ሰበር ዜና! የአገዛዙ ወታደሮች በምስራቅ ወለጋ ዞን አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት 37 የአማራ ተወላጆች ተገደሉ! ትናንት በስቲያ መጋቢት 06/2016 ዓ/ም እኩለ ቀን ገደማ ጀምሮ እስከ ዛሬ መጋቢት 08 ድረስ በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ የአገዛዙ ኃይሎች በከባድ መሣሪያ በመታገዝ በከፈቱት ጥቃት ህፃናትና አረጋውያን እንዲሁም ነፍሰጡር እናቶችን ጨምሮ እስካሁን ቁጥራቸው በውል የታወቀ 37 የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን ነው የአማራ ድምፅ ሚድያ የአከባቢው ነዋሪዎችን በማነጋገር ለማረጋገጥ የቻለው። ጥቃቱ የተከፈተው በአንዶዴ ዲቾ ቀበሌ ስር በሚገኙ ሻሾበር አቦ፣ ደምቢባና ማርያም ሰፈር በተባሉ አከባቢዎች ሲሆን፡ ከግድያ የተረፉት ነዋሪዎች የተቃጣባቸውን ማንነት ተኮር ጥቃት ለመመከት ትንቅንቅ ላይ መሆናቸው ተመላክቷል። ከተገደሉት መካከል አቶ አወቀ ይበልጣልና አቶ ዳምጠው የተባሉ የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ፈኔ አስናቀ እና ሀብቴ አስናቀ የተባሉ በግብርና ስራ ላይ የነበሩ ወጣቶች እንደሚገኙበትም ተጠቁሟል። በተመሳሳይ በላይነህ አንዱአለም የተባለ ወጣት በትናንትናው እለት ሞተር ሳይክል በማሽከርከር ላይ እንዳለ ከአገዛዙ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተመቶ ህወቱ ማለፉም ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በአማራ ክልል ተጠልለው የነበሩና ተፈናቅለው ወደ መጡበት አከባቢ በቅርቡ እንዲመለሱ ከተደረጉት መካከልም በአገዛዙ ኃይሎች ጥቃት የተገደሉ መኖራቸው ተሰምቷል። በአማራ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች በነበሩ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ባሉበት እንዲነሱ ተደርገው ተፈናቅለው ወደ ነበረበት የወለጋ አከባቢ ከተመለሱት መካከል በአንዶዴ ዲቾ ቀበሌ ልዩ ስሙ አልባት ማርያም በተባለ ቦታ በተፈፀመባቸው ጥቃት መገደላቸውን ነው የአይን እማኞች ለአማራ ድምፅ ሚድያ ያረጋገጡት። ከሦስት አመታት በፊት ጀምሮ መንገዶች ተዘጋግተውበት መውጫ መግቢያ አጥቶ በረሃብና በህክምና እጦት ሲንገላታ የነበረው ይህ የምስራቅ ወለጋ አማራ ማህበረሰብ፡ ያለፈው አመት ህዳር ወር ላይ የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ከፍተውበት በነበረው ጥቃት ከ350 በላይ የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፉ የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ የአማራ ድምፅ ሚድያ በወቅቱ መዘገቡ አይዘነጋም። በተመሳሳይ ከሁለት ቀናት በፊት ጀምሮ በኦሮሞ ብልፅግና የበላይነት ለሚዘወረው የአገዛዝ ስርዓት እያገለገለ በሚገኘው መከላከያ ሰራዊቱ በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጥቃት ተከፍቶባቸዋል። የአንዶዴ ዲቾ ቀበሌ ነዋሪዎች በሆኑ የአማራ ተወላጆች ላይ ከተከፈተው ጥቃት ጋር ተያይዞ፡ አንገር ጉቲን ከተማን ጨምሮ በዙሪያው ባሉ በጊዳ አያና ወረዳ፣ በጊዳ ኪረሙ፣ በጉቶ ጊዳ፣በሊሙ በገሊላና በሲቦስሬ ወረዳዎች እንዲሁም ለምስራቅ ወለጋ አጎራባች በሆነው በሆሮ ጉድሩ ዞን ስር በሚገኙ በአቤ ደንጎሮ ወረዳ፣ በጉዳያ ቢላ፣ በአሙሩ እና በጃርዴጋ ጃርቴ ወረዳ ከባድ ውጥረት መንገሱንም የአማራ ድምፅ ሚድያ ካሰባሰበው መረጃ ለማረጋገጥ ችሏል። ——- የአማራ ድምፅ ሚድያ

Source: Link to the Post

Leave a Reply