ሰዎች በቤት ወስጥ በሚጠቀሙባቸው የሴራሚክ ምንጣፎች ለአደጋ እየተጋለጡ መሆኑ ተደጋግሞ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ለመሆኑ በግዥ ወቅት ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል?

የቤት ውስጥ ዲዛይን ከሚያካትታቸው ነገሮች ውስጥ በጥቂቱ የቀለም ምርጫ፣ የመብራት አጠቃቀም፣የቤት ውስጥ መገልገያና ልዩልዩ ቁሳቁሶች አመራረጥና አጠቃቀም፣ የወለልና የጣራ ሽፋን አመራረጥ ይገኙበታል።

የወለል ሽፋን ማለት የአንድ ህንፃ መሠረታዊ መዋቅር ካለቀ በኋላ ወለሉ ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆን በወለሉ ላይ የሚነጠፍ ማንኛውም አይነት ቁሳቁስ ሊሆን ይችላል። ከቁሶቹ መካከል ሴራሚክን መጥቀስ ይቻላል።

ሰራሚክ መሬት ላይ ከምንጠቀማቸው የወለል ንጣፍ አንዱ ነው።
በገበያው ላይም ተመራጭነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ይነገራል።
ሴራሚክን ተመራጭ ከሚያደርገው ጠባይ አንዱ በላዩ ላይ አቧራንና ብናኝን የመሠብሠብ ባህርይ ስለሌለው ለማፅዳት አመቺ በመሆኑ ነው።

ወይዘሮ ማራኪ ተጠምቀ የግንባታ ንድፍና የቤት ውስጥ የስነ ውበት ባለሙያ ናቸው።

ለተሠራው ዲዛይን አግባብ የሆነና ለአጠቃቀም ምቹ የሆነ የወለል ሽፋን ለመምረጥ ያስችለን ዘንድ እነዚህን ነጥቦች ማገናዘብ አስፈላጊ ነው ሲሉ ባለሙያዋ ተናግርዋል።

1፤ህንፃው ወይም ቤቱ ከተሠራበት የዲዛይን ሃሳብ ጋር የተመረጠው የወለል ሽፋን አግባብነት፡፡

2፤ የተመረጠው ዕቃ ጥንካሬ ለእድሳት እንዲሁም በወለል ላይ ለመግጠም አመቺ መሆኑ እናም በቀላሉ መፀዳት መቻሉ፡፡
3፤ የዕቃው ዋጋ
4፤ የወለል ሽፋኑን የምንጠቀምበት የክፍል ወይም የአገልግሎት አይነት ለምሳሌ (ለሳሎን፣ለመኝታ ቤት፣ለመታጠብያ ቤት፣ ለመሰብሰብያ አዳራሽ፣ለህክምና ቦታ……)
5፤ የተመረጠው የወለል ሽፋን በአካባቢው ካለው የአየር ንብረት ጋር የሚስማማ መሆኑ መታየት አለበት ብለዋል፡፡

6፤ ተጠቃሚዎችን ለአደጋ የማይዳርግ መሆኑ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሊሆን እንደሚገባ ተጠቅሷል።

ብዙ ጊዜ ሰዎች ቀልባቸዉ የወደደዉን እየገዙ ይሄዳሉ፤ያ ደግሞ ከፍተኛ አደጋን እያስከተለ ሰዎችን ለተለያዩ የአካል ጉዳት ሰለባ እንደሚዳርጋቸው
እንደ ባለሙያ ተደጋጋሚ መረጃ እንደሚደርሳቸዉ ገልጸዉ ፤ማህበረሰቡ ቢጠቀማቸዉ ያሉትን አንስተዋል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ በብዙ የሴራሚክ አቅራቢዎች ጋር በብዛት የሚታወቀው” ማት “ሴራሚክ በመባል የሚጠራው ነው፡፡
ነገር ግን ሌሎችም እንደ ሱፐር ማት ፣የማንሸራተት አቅሙ መካከለኛ የሆነ ፣ምንም የማያሸራትት ሴራሚኮች በገበያዉ ላይ አሉ።

በምግብ ማብሰያ ፣በመታጠቢያ፣ በመፀዳጃ፣ በሳሎን ቤት እንዲሁም ክብደት ተሸካሚ በሆኑ ስፍራዎች ለምሳሌ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ላይ ማት ሴራሚክ ብንጠቀም የተሻለ ነው ነው ብለውናል።

ሌላኛው ግሎሲ የሚባለው የሴራሚክ አይነት ሲሆን በጣም አንፀባራቂ ለአይን ማራኪ ነው። ብዙ ጊዜ ሰዎች ቢጠቀሟቸው የተሻለ የሚሆነውና የሚመከረው በመታጠቢያ እና በክችን ቤት ግርግዳ ላይ ነው ተብሏል።

ጥንቃቄ በሚሹ ህፃናት፣ትልልቅ ሰዎች ባሉበት ስፍራዎች ከደህንነታቸው አኳያ ማት ወይንም የማያሸራትተውን የሴራሚክ አይነት እንዲጠቀሙ ይመከራል ተብሏል።

ውሃን ወደ ውስጥ ሳያስገባ የመከላከል አቅሙ፣ በቀላሉ መጠገንና መፀዳት መቻሉ፣ በዋጋ ርካሽ መሆኑና አንፃባራቂ የሆነ ጥንካሬው ከተፈለገ ደግሞ ፒቪሲን መጠቀም ተመራጭ ያደርገዋል።

ሁልግዜም ባይሆን ከፍተኛ የሆነ የጥራት መጠን ያለው የፒቪሲ የወለል ሽፋን ወፍራም ሲሆን የላይኛው ክፍሉም እጅግ ጠንካራና ጫናን መከላከል የሚችል ነው።

ይህ የወለል ሽፋን በሚመረትበት ግዜ የውጭ ገፅታው እንጨት፣ ድንጋይ፣ሴራሚክን ወዘተ እንዲመስል ተደርጎ ሊሠራ ወይም ሊመረት እንደሚችል በመጥቀስ ሰዎች በሚገዙበት ወቅት ለውበትም ሆነ ለደህንነት ባለሙያን ቢያማክሩ የተሻለ መሆኑን ባለሙያዋ ጠቁመዋል፡፡

በልዑል ወልዴ

የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply