ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በ60 ሚሊዮን ዶላር ለሚገነባው ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የለማ መሬት በኪራይ ተረከበ

ሐሙስ መስከረም 5 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በሰኔ ወር 2013 በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ህጋዊ ፍቃድ ተቀብሎ ወደሥራ የገባው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በ60 ሚሊዮን ዶላር ለሚገነባው ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የለማ መሬት በኪራይ ተረክቧል።

ዛሬ መስከረም 05 ቀን 2015 ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራርመዋል።

በሥምምነቱ መሰረት፤ ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ በኮርፖሬሽኑ ሥር ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የመረጃ ማዕከል መጠቀም የሚችል ሲሆን፤ 60 ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ የሚያፈስበት እና የራሱን ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል የሚገነባበት በአይሲቲ ፓርክ የሚገኝ 10 ሺህ ካ.ሜ የለማ መሬት በኪራይ ተረክቧል፡፡ በዚህም ከ56 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደሚፈጠር ተነግሯል፡፡

የኢትጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳንዶካን ደበበ፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለው ተሳትፎ አገሪቱ የወጠነችውን የዲጂታል ኢትዮጵያ እቅድ እውን ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር የገባው ሥምምነት ተፈጻሚ እንዲሆን አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግም ሳንዶካን አረጋግጠዋል፡፡ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በአገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ አማራጭ የቴሌኮም ኦፕሬተር በመሆን የተቀላቀለ ካምፓኒ ሲሆን፤ በቅርቡ በምስራቅ እና ሰሜን የአገሪቱ ክፍሎች ባሉ አራት ከተሞች የሙከራ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ እስከ መጪው ሚያዝያ ወር ድረስ በ25 ከተሞች አገልግሎቱን ለማዳረስ ማቀዱም ተነግሯል፡፡

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዋር ሳኡሳ ኮርፖሬሽኑ ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ ካምፓኒው ከኮርፖሬሽኑ ጋር ወደፊት ከሚሰራቸው ብዙ ሥራዎች መካከል ይህ ኢንቨስትመንት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሚገነባው የመረጃ ማዕከል ቲር 3 ሲሆን፤ ለዲጂታል ኢትዮጲያ ግንባታ መሰረት የሚጥል እንደሆነ አንዋር ተናግረዋል፡፡ የሚገነባው የመረጃ ማዕከል በዋናነት አገልግሎት የሚሰጠው ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ቢሆንም ለሌሎች ተቋማትም አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆኑን መግለጻቸውን ኢትዮ የንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም በፓርኩ ያለውን ነባሩን የመረጃ ማዕከል የሚያዘምን (አፕግሬድ) የሚያደርግ ግንባታ መሆኑንም አንዋር ተናግረዋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply