ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገር አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩን በማከናወን ላይ ነው

ሐሙስ መስከረም 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገር አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩን በአዲስ አበባ ” ወዳጅነት አደባባይ ” በአሁን ሰዓት በማከናወን ላይ ይገኛል።

በኩባንያው የአገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች፣ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለአክሲዮኖች፣ የአጋር ድርጅቶች እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዋር ሱሳ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ ኩባንያው አግልግሎቱንበአዲስ አበባ በመጀመሩና እና አገራዊ አገልግሎት ማስጀመሪያ ዝግጅቱን ለማካሔድ በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባደረጉት ንግግር፤ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት መጀመር ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን የብልጽግና ጉዞአችን ሞተር አድርገን የመንቀሳቀሳችን ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው፥ የሳፋሪ ኮም በኢትዮጵያ አገልግሎት መጀመሩ ቀጠናዊ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡በተጨማሪም በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ለኩባንያው በሞባይል የገንዘብ ዝውውር “ሞባይል መኒ” እንዲያከናውን መፈቀዱን አስታውቀዋል።

ከኢትዮጵያ ፌዴራዊ መንግሥት በሐምሌ 2013 ኹለተኛውን ኹለገብ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪነትን ፈቃድ ያገኘው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ እስካሁን አዲስ አበባን ጨምሮ በ11 ከተሞች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያው በአንድ ወር ውስጥ 200 ሺሕ ደንበኞችን ማፍራቱን ያስታወቀ ሲሆን፤ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ ጀምሮ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉን ተናግሯል፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥም በ300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ 500 የኔትወርክ ማዕከላትን እና ኹለት የዳታ ማዕከላትን መገንባቱን አስታውቋል፡፡

The post ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገር አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩን በማከናወን ላይ ነው first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply