ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከነሀሴ ወር ጀምሮ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ

በድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያ አገልግሎቱን እንደሚጀምርም ገልጿል

ሐሙስ ሰኔ 30 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከነሀሴ ወር 2014 ጀምሮ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

የድርጅቱ የውጭ ጉዳዮች እና ቁጥጥር ሀላፊ ማቲው ሀሪሰን እንዳሉት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከአንድ ወር በኃላ የቴሌኮም አገልግሎት ለደንበኞች መስጠት ይጀምራል።

ድርጅቱ የመጀመሪያ አገልግሎቱን በድሬዳዋ ከተማ የሚጀምር ሲሆን፤ እስከሚቀጥለው ሚያዝያ 2015 ድረስ ለ25 ከተሞች የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት እቅድ ማስቀመጡን አስታውቋል።

ድርጅቱ ከዚህ በፊት የቴሌኮም አገልግሎቱን ሚያዝያ 1 ቀን 2014 ለመስጠት እቅድ የነበረው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ተግባር አለመግባቱን አስታውቋል።

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተጀመረው የቴሌኮም መሰረተ ልማት ኪራይ ዋጋ ላይ ከስምምነት አለመድረስ፣ የኔትወርክ ዝርጋታ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ሥራ በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ እና ሌሎች ምክንያቶች ተቋሙ ባሰበው ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር እንቅፋት እንደሆነበት ተገልጿል።

ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ በ07 መነሻ መለያ ቁጥር አገልግሎት እንደሚሰጥ ከዚህ በፊት መናገሩ ይታወሳል።

የጽሁፍ አገልግሎት፣ የዳታ፣ የድምጽ በአገር ውስጥ እና አለም አቀፍ የቴሎኮም አገልግሎቶችን ይሰጣል ያሉት ቺፍ ኦፊሰሩ ከሰኔ በኋላ ደግሞ ኹሉንም የቴሌኮም አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚጀምርም መግለጹ ይታወሳል።

እንዲሁም ድርጅቱ በአዲስ አበባ፣ አዳማ እና ድሬዳዋ ከተሞች የመረጃ ማዕከል መገንባቱ ያሳወቀ ሲሆን፤ እስካሁን ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ በኢትዮጵያ ወጪ ማድረጉንም ማስታወቁን አል አይን ዘግቧል።

በአጠቃላይ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ውስጥ ለግማሹ ህዝብ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት እቅድ እንዳለው የገልጸው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ውስጥ ደግሞ 98 በመቶ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አገልግሎት የመስጠት እቅድ እንዳለውም አስታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply