ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራውን በድሬዳዋ ከተማ መጀመሩን አስታወቀ

በከዚራ፣ መስቀለኛ እና ኮርኔል ያሉ ሦስት የሽያጭ ማዕከሎቹ ለሲም ካርድ ሽያጭ ምዝገባ፣ ለስልክ ቀፎዎች ግዢ እና ልዩ ልዩ የደንበኞች ድጋፍ ለመስጠት ክፍት እንደሚሆኑም ገልጿል

ሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት መጠነ ሰፊ የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራ በድሬዳዋ ከተማ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ይህ የደንበኞች የሙከራ ምዕራፍ ኩባንያው በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎቱን ለመስጠት ከሚዘጋጅበት ጊዜ አስቀድሞ በተለያዩ ክልሎች እና ከተሞች የኔትወርክ እና የአገልግሎት ጥራቱን በተጠናከረ ኹኔታ የሚፈትሽበት ወቅት መሆኑም ተገልጿል።

በድሬዳዋ ከተማ የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራ በ2G፣ 3G እና 4G ኔትወርኮች የሚካሔድ ሲሆን፤ ደንበኞች በ07 በሚጀምረው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መስመር የስልክ ቁጥሮቻቸውን መርጠው ሲም ካርድ መግዛት ይችላሉ ተብሏል፡፡

ደንበኞች የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሲም ካርዶች የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መለያ ከተለጠፈባቸው መደብሮች እና ሱቆች ማግኘት የሚችሉ ሲሆን፤ ኔትወርኩን ለአንድ ወር ያህል እንዲሞክሩት የሚረዳ የደንበኝነት ማስጀመሪያ የዳታ፣ የድምጽ እና የጽሁፍ መልዕክቶች ጥቅል እንደሚያገኙም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የደንበኝነት ማስጀመሪያ ጥቅሉ በሚያልቅበት ጊዜ፤ ደንበኞች የአየር ሰዓት ከሽያጭ ማዕከላት ወይም መለያ ከተለጠፈባቸው መደብሮች እና ሱቆች በመግዛት መሙላት እና አገልግሎቶቻችንን መጠቀም መቀጠል እንደሚችሉም ተነግሯል፡፡

በከዚራ፣ መስቀለኛ እና ኮርኔል ያሉ ሦስት የሽያጭ ማዕከሎቻችን ለሲም ካርድ ሽያጭ ምዝገባ፣ ለስልክ ቀፎዎች ግዢ እና ልዩ ልዩ የደንበኞች ድጋፍ ለመስጠት ክፍት እንደሚሆኑም ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ አገልግሎት በሚጀምረው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሙከራ ኔትወርክ ደንበኞች ዳታ መጠቀም፣ ጥሪዎች እና የጽሁፍ መልዕክቶችን ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ከኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ጋር መለዋወጥ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ጥሪዎችን ማድረግ ይችላሉ ተብሏል፡፡

ደንበኞች ለማንኛውም የደንበኞች ድጋፍ አገልግሎቶች በጥሪ ማዕከሉ በተለያዩ ቋንቋዎች (አማሪኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሱማሊኛ፣ ትግሪኛ እና እንግሊዝኛ) የማግኘት አማራጭ የሚኖራቸው ሲሆን፤ የደንበኞች አገልግሎት ሠራተኞችን 700 ላይ በመደወል ሊያናግሯቸው እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡

ይህ የድሬዳዋ ከተማ የደንበኞች ሙከራ እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ድረስ በ25 ከተሞች ከመንግሥት፣ ከንግድ ድርጅቶች፣ ከየአካባቢው ማህበረሰቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የምናካሒደው ኔትወርካችንን ወደ ሥራ የማስገባት ሒደት አካል መሆኑን ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply