ስለሆነም ጾም የተጋድሎና የሙዓት ሜዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የምንታገለውም ልቡሰ ሥጋ ሰውን ሳይሆን ረቂቅ ፍጡር የሆነው ሰይጣን በሰው አድሮ የሚነዛውን አጥፊ ሐሳቡንና ድርጊቱን ነው፡፡ ከዚ…

ስለሆነም ጾም የተጋድሎና የሙዓት ሜዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የምንታገለውም ልቡሰ ሥጋ ሰውን ሳይሆን ረቂቅ ፍጡር የሆነው ሰይጣን በሰው አድሮ የሚነዛውን አጥፊ ሐሳቡንና ድርጊቱን ነው፡፡
ከዚህም ጋር ሰውነታችን ለዚህ ክፉ መንፈስ ታዛዥ እንዲሆን የሚገፋፉ ጥሉላት መባልዕትን መተው፤ ኃይለ ሥጋን መቈጣጠር፤ ኃይለ መንፈስን ደግሞ ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡ በጾም ወቅት የተራቡትን ማጉረስ የታረዙትን ማልበስ የተበደሉትን መካስ፣ ፍትሕና ርትዕ በማኅበረ ሰብ ውስጥ ማንገሥ ያስፈልጋል፡፡

በጾም ወቅት ኅሊናችን ማሰላሰል ያለበት ሰው ምን አለ? ወይም ምን አደረገ? በሚለው ሳይሆን እግዚአብሔር በፊቱ ምን ዓይነት ሰው እንድንሆንለት ይፈልጋል? በሚለው ላይ ነው፡፡

ስለዚህ ጾማችን በዚህ መንፈስ የተቃኘ ፍቅረ፣ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን ማእከል ያደረገ፣ መጠራጠርንና አለመተመማንን ያስቀረ፣ የተለያዩትን ያቀራረበ፣ የተሳሳቱትን ያረመ በአንጻሩ ደግሞ ሁላችንን በሰላምና በፍቅር አንድ አድርጎ ያስተሳሰረ ይሆን ዘንድ በዚህ መንፈስ ተነቃቅተን እንድንጾመው አባታዊ ጥሪያችንን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም፤
በሀገራችን እየታየ ያለው የሰላም ጭላንጭልና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ዝንባሌ በእጅጉ ጠቃሚና ለሁለንተና ልማታችንና ለዕድገታችን እንደዚሁም ለተሟላ አንድነታችን ጠቃሚነቱ የጎላ ስለሆነ እግዚአብሔር ለዘለቄታው እንዲያሳካልን ከልብ እንድናዝንና ወደ አምላካችን በተመሥጦ እንድንጸልይ በአጽንዖት በማሳሰብ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የጾም ወራት ያድርግልን!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስምወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Source: Link to the Post

Leave a Reply