ስለ ራያ አላማጣ ግጭት እስካሁን የወጡ መረጃዎች፡-አብን፣ የሕወሃት ኃይሎች በአማራ ሕዝብ ላይ “አራተኛ ዙር” ጥቃት ከፍተዋል ሲል ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የፌዴራሉ መንግሥ…

ስለ ራያ አላማጣ ግጭት እስካሁን የወጡ መረጃዎች፡-

አብን፣ የሕወሃት ኃይሎች በአማራ ሕዝብ ላይ “አራተኛ ዙር” ጥቃት ከፍተዋል ሲል ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የፌዴራሉ መንግሥትና የአማራ ክልላዊ መንግሥት ሕወሃት በአማራ ሕዝብ ላይ የከፈተውን ሌላ ዙር ጥቃት ባስቸኳይ እንዲያስቆሙ አብን በመግለጫው ጠይቋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት የሕወሃትን ጥቃት እንዲመክትም ጥሪ ያቀረበው አብን፣መንግሥት የሕወሃትን ጥቃት በዝምታ ከተመለከተ፣ ድርጊቱ “የኹሉ ነገር መፍረሻና ማፍረሻ” እንዲኾን ፈቅዷል ማለት ነው ሲልም ይገልጻል።
አብን ይህን መግለጫ ያወጣው፣ የሕወሃት ኃይሎች በራያ አላማጣ አካባቢ አንዳንድ ቦታዎችን እየተቆጣጠሩ ስለመኾኑ በተሰማ ማግስት ነው።

በሌላ በኩል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ በደቡብ ትግራይና በሌሎች በኃይል የተያዙ የትግራይ ግዛቶች ባኹኑ ወቅት የተፈጠረው ክስተት በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወይም በሕወሃት ወይንም በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የተፈጠረ ግጭት አይደለም በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

አቶ ጌታቸው ፣ ክስተቱ ኹለቱ ወገኖች የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እያደረጉት ያለውን አወንታዊ ግንኙነት ለማደናቀፍ የፈለጉ የስምምነቱ ጠላት የኾኑ ኃይሎች የፈጠሩት ነው በማለትም አስፍረዋል፡፡

ከሩቅም ከቅርብም የግጭት ማቆም ስምምነቱ ጸር የኾኑ ኃይሎች ጦር እየሰበቁ መኾኑን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ ብቸኛው አዋጭ መንገድ ግን ሰላም ነው ብለዋል።

ኹለቱ ወገኖች ችግሮችን ለመፍታትና የሚስማሙባቸውን ጉዳዮች ለማጎልበት አዲስ አበባ ውስጥ ስብሰባ ላይ እንደኾኑም አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል።

አቶ ጌታቸው በአካባቢው ተፈጠረ የተባለውን ግጭት የስምምነቱ ጸር የሆኑ አካላት ናቸው የፈጠሩት ከማለት በስተቀር በስም አልጠቀሱም፡፡

በጉዳዩ ላይ የፌደራል መንግስቱም ሆነ የአማራ ክልል መንግስት እስካሁን የሰጡት ምላሽም ማብራሪያም የለም፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሚያዝያ 08 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply