
ስለ ሰፊው የአማራ ህዝብ ሲታገል በክብር የተሰዋው የፋኖ ሞላጃው ሙላው እናት አረፉ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ስለ ሰፊው የአማራ ህዝብ ብሎም ስለ ሀገር ሲታገል ህዳር 16/2009 ዓ/ም በጎንደር ጠገዴ ወረዳ አዴት ቀበሌ በክብር የተሰዋው የፋኖ ሞላጃው ሙላው እናት ወ/ሮ እናና ከበደ አርፈዋል። ወ/ሮ እናና ከበደ ጀግና የወለዱ ብቻ ሳይሆኑ እሳቸውም በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍ በማውገዝ፣ ለውጥ ናፋቂው ጀግናው ልጃቸው ሞላጃው ሙላው ብሎም ታጋይ ጓዶቹ የሚያደርጉትን የአርበኝነት ትግል በመደገፍ የሚታወቁ ጀግና የጀግና እናት መሆናቸው ይታወቃል። በአርበኛ ልጃቸው ሞላጃው ሙላው በክብር መሰዋዕት ክፉኛ በሀዘን የተጎዱት ወ/ሮ እናና ከበደ በተለያዩ ጊዜያት የጤና ችግር እያጋጠማቸው መቆዬቱ ይታወሳል። በልጆች እና በተወሰኑ በጎ ፈቃደኛ ፋኖዎች እና ወገኖች ትብብር እስከ ጎንደር ድረስ በመመላለስ የህክምና ክትትል ተደርጎላቸው፣ የጤና መሻሻልም አሳይተው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ማዕከላዊ አርማጭሆ ወረዳ ማሰሮ ደንብ ከተማ መመለሳቸው ይታወቃል። ይሁን እንጅ በሀዘን እና በህመም ብዙ የተንገላቱት የጀግናው እናት ወ/ሮ እናና ከበደ በሚኖሩበት ማሰሮ ደንብ ከተማ የካቲት 11/2015 ከቀኑ 12 ሰዓት ገደማ ህይወታቸው የማለፉ አሳዛኝ ዜና ተሰምቷል። የወ/ሮ እናና ልጅ ጀግናው ሞላጃው ሙላው ሀገራችን ለውጥ ያስፈልጋታል፤ የአማራ ህዝብ ተበድሏል፣ የህወሓት መራሹ ስርዓት ሀገሬን እየጎዳት ነው ብሎ ገና በለጋ እድሜው ነበር ከባርነት ነፃነት ወይም ሞት በማለት ልክ እንደ እነ አርበኛ ዋዋ ጎቤ መልኬ፣ ሙሃቤ በለጠ፣ቃቁ አወቀ፣ ደሳላኝ አዱኛ እና ሌሎች አያሌ የአርማጭሆ ጀግኖች ስለ ሰፊው የአማራ ህዝብ ብሎም ስለ ሀገር ሲል ክቡር የህይወት መስዋዕት በመክፈል በደሙ የማይሞት ታሪክ ጽፎ ማለፉ ይታወሳል፡፡ ስርዓተ ቀብራቸውም የካቲት 12/2015 በማሰሮ ደንብ ከተማ ወዳጅ ዘመድ፣ የጀግናው ፋኖ ሞላጃው ሙላው የትግል ጓዶች፣ የአርማጭሆ፣ የማሰሮ ደንብ እና የአካባቢው ማህበረሰብ በተገኘበት የሚፈጸም ይሆናል። ነፍስ ይማር!
Source: Link to the Post