#ስለ #ቼክ ማወቅ ያለባችሁ ወሳኝ ነጥቦች:- ጠበቃና የህግ አማካሪ የሆኑት አቤል ዘውዱ በቼክ ገንዘብ ሊሰጣችሁ ወይም ቼክ ልትፈርሙ ስለምትችሉ ቀጣዮቹን ቼክን የሚመለከቱ ወሳኝ ነጥቦ…

#ስለ #ቼክ ማወቅ ያለባችሁ ወሳኝ ነጥቦች:-

ጠበቃና የህግ አማካሪ የሆኑት አቤል ዘውዱ በቼክ ገንዘብ ሊሰጣችሁ ወይም ቼክ ልትፈርሙ ስለምትችሉ ቀጣዮቹን ቼክን የሚመለከቱ ወሳኝ ነጥቦች እወቁ ይሏችኋል፡፡

ጠበቃና የህግ አማካሪው አቤል ቼክ ማለት ገንዘብን ተክቶ የሚያገለግል ተላላፊ የገንዘብ ሰነድ ወይንም በእንግሊዘኛው commercial instrument ሲሉ ይገልጹታል።

# ቼክ ሊፈርም የሚችለው በአንድ ባንክ ውስጥ ተንቀሳቃሽ ሂሳብ ያለው ሰው ነው፡፡

#ድርጅት ከሆነ ደግሞ ፈራሚው በድርጅቱ ቼክ ላይ የመፈረም ስልጣን የተሰጠው መሆን አለበት ይላሉ ጠበቃና የህግ አማካሪው፡፡

# ቼክ ከመቀበላችን በፊት በቼኩ ላይ በጥንቃቄ ማየት ያሉብን ነጥቦች

-የሚከፈለው የገንዘብ መጠን በአሀዝና በፊደል መፃፉን
-የሚከፈለው ሰው ስም እና የባንኩ ቅርንጫፍ መፃፉን
-ቼኩን የሰጠው ሰው ፊርማ መኖሩን
-ቼኩ የተፃፈበት ቀን እና ቦታ መኖሩ ማረጋገጥ የግድ አስፈላጊ መሆኑን የንግድ ህግ አንቀፅ 827 ይደነግጋል።

#ይህ ካልሆነ ሊፈጠር የሚችለው ምንድነው?

-ቼኩ ለማን እንደሚከፈል ስም ካልተጠቀሰበት ማንኛውም ቼኩን ይዞ የቀረበ ሰው ይከፈለዋል።

-ቼኩ በስሙ የተፃፈለት ሰው ወይም በትዕዛዝ የሚል ካለበት ደግሞ በቀላሉ ከጀርባው በመፈረም ለሌላ ሰው ሊያስተላልፈው ይችላል።
ያም ሰው በጀርባው ፈርሞ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ ይችላል፡፡

-የገንዘብ መጠኑ ያልተጠቀሰበትን ቼክ ፈርሞ መስጠት አደገኛ ነው ፡፡

ቼኩ የተፃፈለት ወይም የተላለፈለት ሰው የፈለገውን ገንዘብ ሊሞላበት የሚችል በመሆኑ ነው ይላሉ ፡፡

#አንድ ሰው ቼኩን መጠቀም የሚችለው ለምን ያህል ጊዜ ነው?

-ቼኩ የሚከፈለው ለባንኩ ለክፍያ በቀረበ ቀን ነው።

– ሆኖም ቼኩ በን/ሕ/ቁ 857 መሠረት የወጣበት ቀን ከግምት ሳያስገባ ቼኩ ላይ ከተፃፈው ቀን ጀምሮ በ6 ወር ውስጥ ለባንኩ ለክፍያ መቅረብ አለበት።

-ቼኩን የሚፈርመው ሰው የክፍያውን ቀን ቼኩን ከፃፈበት ወይም ቼኩን ካወጣበት ቀን ወደፊት ወይም ወደ ኋላ ሊያደርገው ይችላል።

#ለምሳሌ:- ዛሬ ቼኩን ሲፅፍ የተፃፈበት ቀን ወደኃላ 7 ወር አድርጎ ቀኑን ቢፅፈው ለክፍያ መቅረብ ያለበት 6 ወር ጊዜ ስላለፈ ባንኩ መክፈልም ሆነ ያልከፈለበትን ምክንያት ለመግለፅ ሳይገደድ ቼኩ ለክፍያ መቅረብ ባለበት ጊዜ ባለመቅረቡ ብቻ ይመልሰዋል፡፡

ዛሬ የሚሰጥህን ቼክ ወደፊት የዛሬ 4 ወር አድርጎ ቀኑ ከተፃፈበት ለክፍያ መቅረብ የሚችለው ከአራት ወራት በኃላ ካለው ቀን ጀምሮ ባለው 6 ወራት ውስጥ ነው፡፡

ስለዚህ ቼክ ተቀባዬች የሚሰጣቸውን ቼክ ገንዘቡን መቀበል ከሚችሉበት ቀን አንፃር በጥንቃቄ የተፃፈበት ቀን ማየት አለባቸው ተብሏል።

-በተለምዶ ‘‘ደረቅ ቼክ’’ የሚባለው ለክፍያ ሲቀርብ በሂሳቡ ውስጥ በቂ ገንዘብ ከሌለው ሲሆን ባንኩ በሚሰጠው ማስረጃ መሰረት ቼክ ሰጪውን ወይም አውጭውን በወንጀል ያስጠይቃል።

እነዚህ ከላይ ያነሳናቸው ህጎች ቼክን የገንዘብ ያህል አስተማማኝ ለማድረግ የተደነገጉ ናቸው።

በመሆኑም ለግብይት ቅልጥፍና እንዲሁም ለገንዘብ እንቅስቃሴ አመቺነት በቼክ መጠቀሙ ከጥሬ ገንዘብ የተሻለ ዘመናዊ አሰራር በመሆኑ ቼክ አስፈላጊና ልንጠቀምበት የሚገባ የገንዘብ ሰነድ ነው ይላሉ ጠበቃና የህግ አማካሪ አቤል ዘውዱ።

ለማንኛውም ቼክ ስንሰጥም ሆነ ስንቀበል ከላይ የተነሱትን ነጥቦች ልብ እንበል ብለዋል ባለሙያው፡፡

በልዑል ወልዴ

ሚያዝያ 05 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply